ኤምሬትስ በጋዛ ሰርጥ ሆስፒታል ልትከፍት ነው
150 አልጋዎች የሚኖሩት ሆስፒታል በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት የቆሰሉ ፍልስጤማውያን ይታከሙበታል ተብሏል
የሆስፒታሉ ቁሳቁሶች በአምስት አውሮፕላኖች ተጭነው ወደ ግብጽ መላካቸውም ተገልጿል
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሀመድ ቢን ዛይድ በጋዛ ፈጣን የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ “ዘ ጋላንት ናይት 3” የተሰኘ ዘመቻ ጀምረዋል።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የቀይ መስቀል ማህበር እና የሀገሪቱ ግብረሰናይ ድርጅቶችን በአንድ የሚያስተባብር ቡድን አዋቅረውም የሰብአዊ ድጋፎች እየተላኩ ነው።
ለፍልስጤማያን ለመድረስ የተመዘገቡ የህክምና ባለሙያዎች እና የቀይ መስቀል ሰራተኞች ወደ ጋዛ እንዲጓዙም አዘዋል ተብሏል።
ኤምሬትስ በጋዛ ሰርጥ የፊልድ ሆስፒታል ለመክፈት መዘጋጀቷም ተገልጿል።
በትናንትናው እለትም ለሆስፒታሉ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን የጫኑ አምስት አውሮፕላኖች ከአቡዳቢ ወደ ግብጽ ማቅናታቸው ነው የተነገረው።
በጋዛ የሚከፈተው የኤምሬትስ የፊልድ ሆስፒታል 150 አልጋዎች ይኖሩታል የተባለ ሲሆን፥ የቀዶ ጥገናን ጨምሮ የተለያዩ ህክምናዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ ግብአቶች ይሟሉለታል።
የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሀመድ ቢን ዛይድ ለፍልስጤም የ20 ሚሊየን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ማዘዛቸው ይታወሳል።
በቅርቡም በጦርነቱ የቆሰሉ 1 ሺህ ፍልስጤማውያን ህጻናት በሀገሪቱ ሆስፒታሎች ህክምና እንዲያገኙ መፍቀዳቸው አይዘነጋም።
በፕሬዝዳንቱ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የጋዛ ጉዳይ “ኤምሬትስ ለፍልስጤማውያን ያላት ታሪካዊ ድጋፍና ወንድማማችነት ማሳያ ነው” ብሏል የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ዋም።