የአረብ ኢምሬት ፕሬዝዳንት የመንግስት ሆስፒታሎች ፍልስጤማዊያን ህጻናት እንዲጠለሉባቸው ወሰኑ
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አልናህያን አንድ ሺህ የፍልስጤም ህጻናት እንዲጠለሉ መወሰናቸው ተገልጿል
የእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት ከተጀመረ 26ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
የአረብ ኢምሬት ፕሬዝዳንት የመንግስት ሆስፒታሎች ፍልስጤማዊያን ህጻናት እንዲጠለሉባቸው ወሰኑ።
ከ26 ቀናት በፊት ለፍልስጤም ነጻነት እዋጋለሁ የሚለው ሀማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።
በጦርነቱ በየዕለቱ ሰዎች እየተገደሉ ሲሆን ከስምንት ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን በእስራኤል ሲገደሉ 1ሺህ 400 እስራኤላዊያን ተገድለዋል።
እስራኤል በጋዛ እና አካባቢው የከፈተችው የአየር እና መሬት ላይ ጥቃት የቀጠለ ሲሆን ንጹህ ፍልስጤማዊያን የጉዳቱ ዋነኛ ሰለባ መሆናቸው ተገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኢምሬት የመንግስት ሆስፒታሎች አንድ ሺህ ፍልስጤማዊያን ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው እንዲስተናገዱባቸው ወስናለች።
የአረብ ኢምሬት ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አልናህያን የመንግስት ሆስፒታሎች ፍልስጤማዊያን እንዲስተናገዱባቸው መወሰናቸውን የኢምሬት ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የአረብ ኢምሬት ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አልናህያን ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ፕሬዝዳንት ሚርጃና ስፖሊያርች ጋር በስልክ ስለ ጋዛ ተጎጂዎች መወያየታቸው ተገልጿል።
ሀገሪቱ ፍልስጤማዊያን ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው በመንግስት ሆስፒታል የህክምና እና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎች ይደረግላቸዋልም ተብሏል።