አረብ ኢምሬት ለሱዳን የ200 ሚሊዮን ዶላር ሰብዓዊ እርዳታ ሰጠች
በሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ለተጎዱ ንጹሀን የሰብዓዊ እርዳታ ማሰባሰብ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/14/258-115127-img-20250214-wa0015_700x400.jpg)
ጉባኤው በኢትዮጵያ ፣ አረብ ኢምሬት ፣ኢጋድ እና አፍሪካ ህብረት በጋራ የተዘጋጀ ነው
አረብ ኢምሬት ለሱዳን 200 ሚሊዮን ዶላር ሰብዓዊ እርዳታ ሰጠች።
በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት እንደቀጠለ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት 30 ሚሊዮን ሱዳናዊያን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።
እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሱዳናዊያን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰብን ዓላማው ያደረገ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት፣ የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ሚንስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።
የጉባኤው አዘጋጅ ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኢምሬት 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች።
የአረብ ኢምሬት ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን በመድረኩ ላይ እንዳሉት በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለከፋ የሰብዓዊ ጉዳት ተዳርገዋል ብለዋል።
ሚንስትሩ አክለውም "ከሁለት ሳምንት በኋላ የረመዳን ጾም ይገባል፣ ሱዳናዊያን ሰላም ይፈልጋሉ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሱዳን የሰብዓዊ መብት ድጋፍ እንዲያዱርግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን ገለጻ የተባበሩት አረብ ኢምሬት በ2024 400 ሚሊዮን ዶላር ለሰብዓዊ ድጋፍ ስታደርግ አሁን ደግሞ ተጨማሪ 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች።
የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዳሉት በሱዳን ያለው የሰብዓዊ ቀውስ በአፍሪካ ካሉት ችግሮች ዋነኛው ነው፣ሴቶች እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች የጥቃቱ ኢላማ ሆነዋል ብለዋል።
ጦርነቱ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ በማስከተሉ ሊቆም ይገባል ያሉት ዋና ጸሀፊው ተፋላሚዎች አሁኑኑ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ተፋላሚዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን እንዲያከብሩ እና ንጹሀንን እንደ ጦርነት መሳሪያ መጠቀም እንደማይገባም ዋና ጸሀፊው አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላለፉት ስድስት ዓመታት ለሱዳን ሰላም ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች ብለዋል።
"ሁሉም ሱዳናዊያን ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ እጠይቃለሁ፣ ኢትዮጵያም እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ ከሱዳናዊያን ጎን ትቆማለች" ሲሉም በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።
አረብ ኢምሬት ከሱዳን ጋር ጥሩ የሚባል ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያላት ሲሆን ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጓም ተገልጿል።