የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኮቪድ-19 የሙከራ ክትባት ወሰዱ
በሀገሪቱ በ3ኛ ደረጃ በሚደረገው የሙከራ ክትባት እስካሁን ከ31 ሺ በላይ በጎ ፈቃደኞች መከተባቸው ተገልጿል
ክትባቱ በደረጃ 1 እና 2 ክሊኒካዊ ሙከራዎች ወቅት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን አንድ ጥናት አመልክቷል
የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኮቪድ-19 የሙከራ ክትባት ወሰዱ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብደላህ ቢን ዛይድ የኮቪድ -19 የሙከራ ክትባት መውሰዳቸው ተገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክትባቱን መውሰዳቸውን የሚያሳይ ፎቶግራፍ በትዊተር ገፃቸው ላይ የለጠፉ ሲሆን “የኮሮና ክትባት ወደ መደበኛው ኑሮ የመመለስ መንገዳችን ነው” የሚል ጽሁፍም አስፍረዋል፡፡
ሼክ አብደላህ ቢን ዛይድ ሲከተቡ-ፎቶ ከትዊተር ገጻቸው
በመንግስት ባለቤትነት የሚተዳደረው የቻይና ናሺናል ፋርማሱቲካል ግሩፕ (ሲኖፋርም) ያበለጸገውን የቻይና ክትባት በሶስተኛ ደረጃ ሙከራ ከ 31,000 በላይ በጎ ፈቃደኞች በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተከትበዋል፡፡
ዘ ላንሴት መጽሔት ላይ ሐሙስ ዕለት የታተመ አንድ ጥናት ክትባቱ በደረጃ 1 እና 2 ክሊኒካዊ ሙከራዎች ወቅት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን እና ክትባቱን የወሰዱ እስከ 80 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ፀረ እንግዳ አካላትን ማምረታቸውን አመልክቷል፡፡
ይሁንና ጥናቱ በ ኮቪድ-19 (SARS-CoV-2) ቫይረስ መያዝን ከመከላከል አንጻር ክትባቱ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ለመገምገም ታስቦ የተዘጋጀ ባለመሆኑ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያረጋግጡ በቂ ፀረ እንግዳ አካላት መመረታቸውን ማረጋገጥ እንደማያስችል ነው የተገለጸው፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጤና ሚኒስትር አብዱልራህማን አል ኦዋይስ ባለፈው ወር የመጀመሪያ ክትባት ተሰጥቷቸዋል፡፡
አል ኦዋይስ ክትባቱን በወሰዱበት ወቅት "ይህንን ክትባት በማቅረብ ለፊት መስመር ጀግኖች ሁሉንም የደህንነት መጠበቂያዎች ለማቅረብ እንፈልጋለን" ብለዋል፡፡ የህክብና ባለሙያዎችን "በስራቸው ተፈጥሯዊ ባህሪ ምክንያት ከሚገጥሟቸው አደጋዎች ሁሉ ልንጠብቃቸው እንፈልጋለን" ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የብሔራዊ ድንገተኛ አደጋዎች አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኦባይድ አል ሻምሲም እንዲሁ ክትባቱን ወስደዋል፡፡
"ይህ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ ክትባት መገኘቱ የሰዎችን ሕይወት ለማዳን አስተዋፅዖ ያደርጋል" ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡
የኤሚሬቶች ስራ አስፈጻሚ ጽ / ቤት ሰብሳቢ ሼክ ካሊድ ቢን መሀመድን ጨምሮ ሌሎች የአቡዳቢ ከፍተኛ ባለስልጣናትም ክትባቱን ወስደዋል፡፡
ዘ ናሺናል እንደዘገበው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባለፉት 24 ሰዓታት 116,470 ምርመራ በማድረግ 1,412 አዲስ የኮሮና ተጠቂዎች መገኘታቸውን ሪፖርት ያደረገች ሲሆን አጠቃላይ የተጠቂዎች ቁጥር 112,849 ደርሷል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት 104,943 ሰዎች ሲያገግሙ 455 ሰዎች እስካሁን ለሞት ተዳርገዋል፡፡ አሁን ላይ በቫይረሱ ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ 8 ሺህ በታች ነው፡፡