ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ ሀገራት ብሪክስን የመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል
የዓለም የምጣኔ-ሀብት ታዳጊ ሀገራት የሆኑት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ 15ተኛውን የመሪዎች ጉባኤ ከዛሬ ማክሰኞ እስከ ሀሙስ ድረስ በጁሀንስበርግ ያካሂዳሉ።
ብሪክስ ስያሜውን ከአባል ሀገራት ስም በምህጻረ ቃል የወሰደ ሲሆን፤ በይፋ የተመሰረተው በጎርጎሮሳዊያኑ 2009 ነው።
ጥምረቱ በአሜሪካ እና በምዕራባውያን አጋሮቿ የሚመራውን የዓለምን ስርዓት ለመቃወም ለአባላቱ መድረክ ለመስጠት ተመስርቷል።
የቡድኑ መጠንሰስ የተጀመረው በሩሲያ ነው።
የአባል ሀገራት መሪዎች በየዓመቱ የሚሰበሰቡ ሲሆን፤ መሪዎቹ የቡድኑን ተለዋጭ ሊቀ-መንበርነት በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይረከባሉ።
ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር አራቱ ሀገራት መስራች አባላት ናቸው።
ደቡብ አፍሪካ ከመስራቾቹ አንጻር አነስተኛ ምጣኔ-ሀብትና የህዝብ ቁጥር ያላት ሲሆን፤ በ2010 በተደረገው የቡድኑ ማስፋፊያ መርሃ-ግብር ብሪክስን ተቀላቅላለች።
የብሪክስ አባላት 40 በመቶ የዓለም ህዝብን የሚሸፍኑና ሲሶውን የዓለም ምጣኔ-ሀብት ይይዛሉ።
ከጂኦ-ፖለቲካ ባለፈ የቡድኑ ትኩረት የምጣኔ-ሀብት ትብብርን እና የባለ ብዙ ወገን ንግድና ልማትን ይጨምራል።
ቡድኑ የሚንቀሳቀሰውም በስምምነት ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ ሀገራት ብሪክስን የመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል።
በደቡብ አፍሪካ ሊቀ-መንበርነት በሚመራው ጉባኤ፤ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ አርጀንቲና፣ አልጄሪያ፣ ቦሊቪያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ግብጽ፣ ኩባ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኮሞሮስ፣ ጋቦን እና ካዛኪስታንን ቡድኑን ለመቀላቀል ከፈለጉ ሀገራት መሀል ናቸው።
አመልካች ሀገራት ብሪክስን በምዕራባውያን ኃያላን የሚመራውን ዓለም አቀፋዊ ስርዓትን ለመገዳደር እንደ አማራጭ ያዩታል።
ሀገራቱ ቡድኑ ልማት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ጥቅሞችን እንደሚከፍት ተስፋ አላቸው።