በመካከለኛው ምስራቅ የደቡብ ኮርያ ሁለተኛዋ ግዙፍ የንግድ አጋር - አረብ ኤምሬትስ
በ2023 ከነዳጅ ውጭ የሀገራቱ የርስ በርስ ንግድ 5.3 ቢሊየን ዶላር ደርሷል
አቡዳቢ እና ሴኡል በአማራጭ ሀይል ግንባታ እና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ትብብራቸውን እያሳደጉ ነው
የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ ትብብር ያሳደጉት አረብ ኤምሬትስ እና ደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው በየአመቱ በማደግ ላይ ይገኛል።
በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ በገቢ እና ወጪ ምርቶች ግብይት ፣ በሀይል አማራጮች ግንባታ እና በሌሎችም ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎች የሀገራቱ ትብብር እየጨመረ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ሀገራቱ ከነዳጅ ውጭ እርስ በእርስ ያላቸው የንግድ ግንኙነት በ2023 5.3 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።
ኤምሬትስ በ2022 ከደቡብ ኮርያ 4.1 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን አስገብታለች፡፡
በተመሳሳይ አቡዳቢ ወደ ሴኡል 886 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ሸቀጦችን ልካለች፤ ይህም ካለፈው አመት በ30 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው ተብሏል።
ሁለቱ ሀገራት በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብርም እያሳደጉ ይገኛሉ።
አረብ ኤምሬትስ ከ2021-2023 ባለው ጊዜ 351.8 ሚሊየን ዶላር በደቡብ ኮሪያ ኢንቨስት ስታደርግ፥ ደቡብ ኮርያ በበኩሏ በኤምሬትስ የ2.7 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንቶች አሏት፡፡
ኬሚካል፣ የተሸከርካሪ አካላት ምርት፣ የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና ሪልስቴት ሀገራቱ በስፋት መዋለ ነዋይ ከሚያፈሱባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በመካከለኛው ምስራቅ የደቡብ ኮርያ ሁለተኛዋ ግዙፍ የንግድ አጋር ነች።
ሴኡል በ2023 ከአረብ ሀገራት ጋር ካደረገችው የንግድ ልውውጥ የአቡዳቢ ድርሻ 20 በመቶ መሆኑንም መረጃዎች ያመላክታሉ።
በተያያዘ ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ ደቡብ ኮርያ በኤምሬትስ ለሀይል አቅርቦት የሚውል የኒዩክሌር ጣቢያ ለመገንባት የ20 ቢሊዮን ዶላር ጨረታ ማሸንፏ ይታወሳል።
በነገው እለት ሴኡል የሚገቡት የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጋር በሚያደርጉት ምክክርም የሀገራቱን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስር በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።