ኤምሬትስ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ በጽኑ አወገዘች
ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አጋርነታቸውን ገልጸዋል
ኤምሬትስ ማንኛውንም አይነት የአመጻ ድርጊትና ሽብርተኝነት በጽኑ እንደምታወግዝ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል
አረብ ኤምሬትስ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ በጽኑ አወገዘች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አጋርነታቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ “በፔንሲልቫኒያ በተፈጸመው ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ዶናልድ ትራምፕ እና ሌሎች ግለሰቦች አጋርነታችን መግለጽ እንፈልጋለን” ብለዋል።
አረብ ኤምሬትስ ማንኛውንም አይነት የአመጻ ድርጊትና ሽብርተኝነት በጽኑ እንደምታወግዝም ነው የተናገሩት።
የ2024ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ዶናልድ ትራምፕ ትናንት በፔንሲልቫኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በተተኮሰባቸው ጥይት በቀኝ ጆሯቸው አካባቢ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የግድያ ሙከራውን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለትራምፕ አጋርነታቸውን እየገለጹ ሲሆን፥ የ78 አመቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በፍጥነት እንዲያገግሙ እየተመኙላቸው ነው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ካወገዙት መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።
የፔንሲልቫኒያውን ጥቃት “አስደንጋጭ” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ትራምፕ ከጉዳታቸው በፍጥነት እንዲያገግሙና ቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የሀገራት መሪዎች በዶናልድ ትራምፕ ላይ ባነጣጠረው የግድያ ሙከራ ምን አሉ? ሊንኩን ተጭነው ያንብቡ