“በትምህርት ላይ ያፈሰስነው መዋዕለ ንዋይ ለስኬታችን መሰረት ነው” - ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የአለም መምህራን ቀንን አስመልክተው የምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል
በአለማቀፍ ደረጃ ከ95 ሚሊየን መምህራን ትውልድን በመቅረጽ ላይ ይገኛሉ
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በሀገሪቱ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን መምህራን አመሰገኑ።
ፕሬዝዳንቱ አለማቀፉን የመምህራን ቀን በማስመልከት በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፥ መምህራን ትውልድን በማስተማርና በማሰልጠን እየተወጡት ያለውን ሚና አድንቀዋል።
ኤምሬትስ ለያዘችው የእድገት ትልም የመምህራን ድርሻ ትልቅ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።
ሀገሪቱ ለትምህርት ያፈሰሰችው መዋዕለ ንዋይ በተለያዩ ዘርፎች ላስመዘገበችው ስኬት መሰረት መሆኑን በመጥቀስም ለመላው መምህራን የእንኳን አደረሳችሁና የምስጋና መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኤምሬትስ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙና በመላው አለም ለሚገኙ መምህራን ተገቢው እውቅና እንዲሰጥ ከዚህ ቀደም አለማቀፍ መድረኮችን ጭምር በማዘጋጀት ትታወቃለች።
የአለም መምህራን ቀን በየአመቱ በፈረንጆቹ ጥቅምት 5 ይከበራል።
ቀኑ በተለይ ከፈረንጆቹ 1994 ጀምሮ በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እውቅና ተሰጥቶት በተለያዩ ሀገራት በመከበር ላይ ይገኛል።
በ1966 በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የተካሄደው በመምህራን ላይ ያተኮረ ልዩ አለማቀፍ ጉባኤ የተጠናቀቀው ጥቅምት 5 መሆኑም በየአመቱ የመምህራን ቀን በዚሁ ቀን እንዲከበር ምክንያት መሆኑ የሚታወስ ነው።
በአለማቀፍ ደረጃ ከ95 ሚሊየን መምህራን በስራ ላይ እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
በ2030 በአለማቀፍ ደረጃ ለማሳካት የተያዘውን የመሰረታዊ ትምህርትን የማዳረስ ግብ ለማሳካት ተጨማሪ 69 ሚሊየን መምህራን እንደሚያስፈልጉ ዩኔስኮ ይገልጻል።
ይሁን እንጂ ከደመወዝ ማነስና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ በየአመቱ ከስራ ገበታቸው የሚለቁ መምህራን ቁጥር አሳሳቢ ሆኗል።