ኢምሬትስ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ያስመዘገበችው ውጤት በአለም አቀፍ ባለሙያዎች ተወድሷል
ሀገሪቱ ከ200 በላይ የውጭ ሀገራት የመጡ ዜጎች በግዛቷ እንዲኖሩ ፈቅዳለች
በጄኔቫ በተካሄደ የበይነ መረብ ሲምፖዚየም፥ ኤምሬትስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ስራዎች ያከናወነችው ተግባር አድናቆትን አግኝቷል
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ በሰብአዊ መብት መስክ በተሰማሩ አለም አቀፍ ባለሙያዎች ተወድሷል፡፡
በአረብ ኢሚሬትስ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ያተኮረ ምክክር ትናንት ከጄኔቫ በበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
ሀገሪቱ በጾታ እኩልነት ፣ የሃይማኖት ልዩነትን በማክበርና በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ ዓለም አቀፍ ሞዴል ልትሆን የምትችል መሆኗን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ኤምሬትስ በተለያዩ ሀገራት ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት የምትሰጠው አፋጣኝ የሰብአዊ አገልገሎትም የሚደነቅ መሆኑን በሲምፖዚየሙ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም አረብ ኢሚሬትስ መሰረታዊ መብቶችን ማለትም እንደ የግለሰብ ነጻነት፣ በጾታ መካከል እኩልነት እና እኩል እድልን በማረጋገጥ፣ የህጻናት፣ የአረጋውያን እንዲሁም የሰራተኛ መብቶችን በመጠበቅ ረገድ ያስመዘገበቻቸው አስደናቂ ውጤቶችም ተነስተዋል።
ሀገሪቱ ህገወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ የምትጫወተው ሚና በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑንም ነው ባለሙያዎቹ ያነሱት፡፡
የአረብ - አውሮፓ የውይይት እና የሰብአዊ መብቶች ፎረም ሊቀመንበር አይማን ናስሪ ፤ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በሰብአዊ መብት አያያዝ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሰፊ አድናቆትን ማግኘቱን ተናግረዋል።
አረብ ኢሚሬትስ ለሶስት ጊዜያት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባል እንደመሆኗ በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ቁልፍ አጋር ሆናለች ሲሉም አክለዋል፡፡
የአለም አቀፉ የዲፕሎማሲ እና የውይይት ምክር ቤት ተባባሪ ዳይሬክተር ዶክተር ኤሪክ ጎዝላን በበኩላቸው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አመራር "የአብርሃም የሰላም ስምምነት" ለመፈረም የወሰደውን እርምጃ አወድሰዋል፡፡
ከእስራኤል መንግስት ጋር የተደረሰው ስምምነት በቀጣናው ዘላቂ ልማትን እና ብልጽግናን የሚያመጣ መሆንን በመጠቆም፡፡
የኤምሬትስ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት
የተባበሩት አረብ ኢምሬት በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዘርፎች እመርታ ማስመዝገቧን በጄኔቫው የበይነ መረብ ውይይት አስታውቃለች፡፡
አረብ ኢምሬትስ ለዚህ ውጤት መብቃቷ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ መርሆዎች ላይ ያላት ተሳትፎ ንቁ መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሳለች፡፡
ሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቷን የፊታችን ግንቦት ወር ላይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት እንደምታቀርብ ይጠበቃል፡፡
ሪፖርቱ ላይ ከ13 በላይ የአረብ፣ የአውሮፓ እና አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና 17 ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸውንም ነው የገለጸችው፡፡
አረብ ኢምሬትስ በሀገሯ ከ200 በላይ ሀገራት የተሰባሰቡ የዓለማችን ዜጎች የሚኖሩባት ሀገር ስትሆን ዜጎች መብቶቻቸው ተረጋግጦላቸው እንዲኖሩ በማድረግ ረገድ ያስመዘገበችው ውጤት ሀገራት በተምሳሌትነት ሊወስዱት ይገባል ተብሏል።