1 ሺህ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው
“ባራካህ”የኑክሌርኃይል የማመንጪያ ፕሮጄክት ስራ መጀመሩን የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የኑክሌር ኢነርጂ ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
ፕሮጄክቱ በአረቡ ዓለም የመጀመሪያ ሰላማዊ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ነው ተብሏል፡፡
የኑክሌር ኃይል ማመንጫው ይፋ የተደረገው ዩኤኢ በፌዴሬሽን ተዋህዳ ከተመሰረተችበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ ነው፡፡
ይህም ዩኤኢ “አይቻልም የሚለውን እንደማታውቅ” ማሳያ ነው ተብሏል።
በፕሮጄክቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአቡ ዳቢው ልዑል አልጋ ወራሽ እና የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን “ባራካ ሰላማዊ ኑክሌር ኢነርጂ ጣቢያ ኤምሬት ዘላቂ የኢኮኖሚ ብልጽግናን ለማሳካት በያዘችው የረጅም ጊዜ ፍኖተ ካርታ መሰረት የተገኘው ታላቅ ስኬት ነው” ብለዋል።
ፕሮጄክቱ በሀገሪቱ የኢነርጂ ዘርፍ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
“ባራካህ” አራት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጫ ዩኒቶች አሉት።
ከአራቱ ዩኒቶች አንዱ ዛሬ ሀይል ማመንጨት የጀመረም ሲሆን 1 ሺህ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።
በቀጣይ ዓመትም ቀሪዎች ሶስቱ ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ነው የተገለጸው።
በኮሪያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን (ኬኤፒኮ) እየተገነባ ያለው “ባራካህ” የኑክሌር የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጫ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ 5 ሺህ 600 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል ተብሏል።
ይህም የዩኤኢን የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎት 25 በመቶ የሚሸፍን ነው።