ሼክ ሃምዳን ምክትል የዱባይ ገዢ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም ናቸው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የፋይናንስ ሚኒስትር ሼክ ሃምዳን ቢን ረሺድ አል መክቱም ማረፋቸው ተሰማ፡፡
ሼክ ሃምዳን የዩኤኢ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ ሞሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም ወንድም ናቸው፡፡
ሼክ ሞሃመድ ቢን ረሺድ ምክትል የዱባይ ገዢ እንዲሁም የዩኤኢ የፋይናንስ ሚኒስትር የሆኑት ወንድማቸው ሼክ ሃምዳን ማረፋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሼክ ሃምዳን እ.ኤ.አ በ1947 ነው በዱባይ የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቸውን በዚያው በዱባይ ተከታትለዋል፡፡
ወደ እንግሊዝ አቅንተውም በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ተምረዋል፡፡
ከዚያ መልስ ከዱባይ ከተማ ማዘጋጃ ሃላፊነት ጀምሮ እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት እና ፋይናንስ ሚኒስትርነት በደረሱ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃዎች ማገልገላቸውን የህይወት ታሪክ መረጃዎቻቸው ያመለክታሉ፡፡