አረብ ኢምሬት ለኮፕ28 ጉባኤ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መበጀታቸውን ገለጹ
በጀቱ የተመደበው የኮፕ28 አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ስኬታማ ለማድረግ ነው
የዘንድሮው የተመድ ኮፕ 28 አየር ንብረት ለውጥ በዱባይ እየተካሄደ ይገኛል
አረብ ኢምሬት ለኮፕ28 ጉባኤ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መበጀታቸውን ገለጹ፡፡
በአረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የኮፕ28 አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ 11ኛ ቀኑን ይዟል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር በመምከር ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ምድራችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስ ጉዳትን መቀነስ የሚያስችሉ ምክክሮች እና ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡
የጉባኤው አስተናጋጅ የተባበሩት አረብ ኢምሬት ለዚህ ጉባኤ ስኬት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን አስታውቃለች፡፡
የኮፕ 28 ፕሬዝዳንት ዳይሬክተር እና ልዩ ተወካይ አምባሳደር ማጂድ አል ሱዌዲ እንዳሉት በጀቱ የአየር ንብረት ለውጥ እና ስነ ህይወት ጥበቃ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
በጀቱ በተለይም በውሃ ውስጥ የነሚገኙ ስነ ህይወት አካላትን ለመጠበቅ መመደቡ የተገለጸ ሲሆን ሌሎች መንግስታት እና ተቋማት ተጨማሪ በጀት እንዲያዋጡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ የኮፕ30 አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን የማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት የገለጹ ሲሆን ተፈጥሮን ለመጠበቅ ተጨማሪ ሀብት እንዲሰባሰብ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
በዓለማችን እየደረሱ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ታዳጊ ሀገራት ከኢንዱስትሪዎቻቸው የሚለቁት የካርበን ጋዝ መጠን በታዳጊ ሀገራት ላይ ከባድ ተጽዕኖ እያደረገ ይገኛል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልም በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር ከተለያዩ አካላት የሚያፈላልግ ፈንድ የተቋቀዋመ ሲሆን ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋሙ እና በቂ ምላሽ እንዲሰጡ ለማድረግ እቅድ ይዟል፡፡
የአለም ሀገራት እና ተቋማት ለዚህ ፈንድ እስካሁን ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ አሰባስበዋል የተባለ ሲሆን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የጉዳት ካሳ ለተጎጂ ሀገራት መክፈል እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡