ኢትዮጵያና አረብ ኤምሬትስ “የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” መርሃ ግብር አስጀመሩ
መርሃ ግብሩ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት የሚያስጨብጥ ተነግሯል
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የ''አምስት ሚሊዮን ኮደርስ'' መርሃግብር ታላቅ እድል ነው ብለዋል
ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ_ኤምሬትስ በዛሬው እለት የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምረዋል።
የ''5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ'' መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተወካዮች በተገኙበት ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም ተጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ዛሬ በይፋ የጀመርነው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ መርሃግብር ታላቅ እድል ነው” ብለዋል።
“አምስት ሚሊዮኖቹ ኮደርስ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን የሚሰጡ ብቻ ሳይሆኑ ለአህጉራችን የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቁም ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ የወደፊት የሚያልሙ አሳቢ ወጣት ዜጎቿ ተስፋ አላት” ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ፤ “ወጣቶች በመርሃግብሩ በመመዝገብ ክሂሎት እንዲያገኙና አለምአቀፍ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ሁሉም እንዲያበረታታ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት ባስተላፉት መልእክትም፤ “ለታላቁ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ትብብር አመሰግናለሁ” ብለዋል።
የ''አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ'' መርሃ ግብር በኢትዮዽያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥታት የተጀመረ የዲጂታል ሥራ ክሂሎቶችን የማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
መርሃ ግብሩ በፈረንጆቹ በ2026 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክሂሎት የሚያስጨብጥ ይሆናል።