አቡዳቢ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ቶን ቆሻሻን ወደ ዘላቂ ምርቶች መቀየሯ ተገለጸ
ቆሻሻዎቹን በማልማት ለአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች ምርትነት ተቀይረዋል ተብሏል
አረብ ኢምሬት 27 የተረፈ ምርት መልሶ ጥቅም ማዋያ ማዕከላት አሏት
አቡዳቢ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ቶን ቆሻሻን ወደ ዘላቂ ምርቶች መቀየሯ ተገለጸ።
የአረብ ኢምሬቷ አቡዳቢ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 3ነጥብ 45 ሚሊዮን ቶን ቆሻሻን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ለተለያዩ ምርቶች መቀየር ተችሏል።
ቆሻሻውን ወደ ጠቃሚ ምርትነት መቀየር የተቻለው በኬሚካሎች አማካኝነት በመቀየር፣ ዳግም ጥቅም ላይ በማዋል ለአካባቢ ጥበቃ እና ለኢኮኖሚ ተስማሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ተብሏል።
የአቡዳቢ ውስጥ ካሉ የተለያዩ ስፍራዎች የተሰባሰበው ይህ ቆሻሻ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው እና ብዙ የቴክኖሎጂ እውቀት የተገኘበት እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ ቆሻሻ ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ የግንባታ ተረፈ ምርቶች ሲሆን ተረፈ ምርቱን ወደ አፈር ለምነት ማስጠበቂያ ምርትነት መቀየር ተችሏል።
የግብርና እና እንስሳት ተረፈ ምርቶችን ደግሞ ወደ አፈር ማዳበሪያነት መቀየር ተችሏል የተባለ ሲሆን ለአካባቢ አየር ተስማሚ እንዲሆኑም መደረጉ ተገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኢምሬት በመላው ሀገሪቱ 27 የቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ ማዕከላት ያሉ ሲሆን ትልቁ ማዕከላት በአልዐይን ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በተለያዩ ሀገራት የሚያዘጋጅ ሲሆን የዘንድሮውን ኮፕ28 ጉባኤ በአረብ ኢምሬት አዘጋጅነት በዱባይ ከአንድ ወር በኋላ ይካሄዳል።