ኤምሬት ተጨማሪ 12 ካራካል የጦር ሄሊኮፕተሮችን ለመግዛትም ተስማምታለች
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች 80 ራፋል ተዋጊ የጦር ጄቶችን ከፈረንሳይ ልትገዛ ነው፡፡
ዩኤኢ ተጨማሪ 12 ካራካል የጦር ሄሊኮፕተሮችን ለመግዛት መስማማቷንም የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኔዔል ማክሮን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
ማክሮን ለደህንነታችን በጋራ እንሰራለን ሲሉ ያላቸውን መተማመን ገልጸዋል፡፡
ዩኤኢ በኢትዮጵያ የምታደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክራ ቀጥላለች
ለነገ የሚሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማበልጸግ፣ ባለራዕይ ስራ ፈጣሪዎቻችንን ለመደገፍ እና በህዋ ጉዳዮች ላይ ከኤምሬት ጋር ለመስራት ትልቅ የኢንቨስትመንት አጋርነትን ፈጥረናልም ብለዋል ማክሮን፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለ2 ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ዩኤኢ ገብተዋል፡፡
የአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ማክሮንን ተቀብለው በዱባይ 2020 ኤክስፖ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ሼክ መሃመድ ከወራት በፊት በፈረንሳይ ጉብኝት አድርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዩኤኢ በፈዴሬሽን ተዋህዳ የተመሰረተችበትን 50ኛ ዓመት በማክበር ላይ ነች፡፡ ይህን ተከትሎም ማክሮን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ መተባበሩ እንደሚቀጥልና ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ ሃገራቸው የበኩሏን እንደምታበረክትም ነው ያስታወቁት፡፡
በሁለትዮሽ የትብብርና በሌሎች የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም የኤምሬት የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡