በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ማድሪድ 15ኛ ዋንጫውን የማሳካት ጉዞው በዶርትመንድ ይገታ ይሆን?
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በሪያል ማድሪድና በቦርሶያ ዶርትመንድ መካከል ይደረጋል
ሪያል ማድሪድ 15ኛ ዋንጫውን ለማሳከት ሲጫወት ዶርትመንድ 2ኛ ዋንጫውን በእጁ ለማስገባት ይፋለማል
የአውሮፓ ሻፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በእንግሊዟ ለንደን ዊንብሌይ ስታዲየም በስፔኑ ሪያል ማድሪድ እና በጀርመኑ ቦርሲያ ዶርትመንድ መካከል ይካሄዳል።
ከፍተኛ ግምት በተሰጠው በዚህ የፍጻሜ ጫዋታ ላይ በበርካቶች እንደሚጠበቀው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን 14 ጊዜ ያነሱት ሪያል ማድሪዶች ለ15 ጊዜ ማሳካት ከቻሉ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ንግስናን አከሊልም ይቀዳጃሉ።
የ1997 ቱአውሮፓ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ያነሱት ቦርሲያ ዶርትመንዶች ማድሪድን መርታት ከቻሉ ዋንጫውን ለሁለተኛ ጊዜ የግላቸው ያደርጋሉ።
ለ33ኛ ጊዜ ሻፒየን በመሆን የስፔን ላሊጋ ዋንጫን ያነሳው ሪያል ማድረድ በአውሮፓ ሻፒየንስ ሊግ ያለ ሽንፈት ለዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ የደረሰ ሲሆን፤ ይህም በክለቡ ታሪክ አዲስ ሪከርድ ነው።
በአሰልጣኝ ካርሎ አንቾሎቲ የሚመሩት ሎስ ብላንኮዎቹ በሻምፒንስ ሊጉ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ በሳንቲያጎ በርናባው ከመመራት ተነስተው ባየር ሙኒክን 2ለ1 በመርታት ነው ለፍጻሜው ጨዋታ የደረሱት።
የጀርመኑ ዶርትመንድም ከማድሪድ በመቀጠል ዘንድሮ በአውሮፓ መድረኮች ካደረገው 11 ጨዋታዎች ውስጥ በአንድ ብቻ ሽንፈትን በማስተናገድ ቀሪውን በማሸነፍ ነው ለፍጻሜው የደረሰው።
የጀርመኑ ክለብ ቦርስያ ዶርትመንድ የፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ፒኤስጂንበድምር ውጤት 2ለ0 በማሸነፍ ፍፃሜ መድረሳቸውም ይታወቃል።
አሰልጣኖች ስለ ጨዋታው ምን አሉ?
ካርሎ አንቼሎቲ
የ64 ዓመቱ ጣሊያናዊው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ የሻምፒየንስ ሊጋ ዋንጫን 6 ጊዜ ማሳት የቻሉ ሲሆን፤ ይህም አራት ጊዜ በአሰልጣኝነት፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ነው።
አንቼሎቲ ስለ ጨዋታው ሲናገሩም፤ “ስሜቱ ከመጀመሪያው ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ በመጀመሪያ እዚህ ለመድረሳችን ደስታ ይሰማናል፤ ቀጥሎም ሃሳብና ስጋት ይከተላል፤ ሆኖም ግን ለሁሉም ነገር ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
አሰልጣኙ አክለውም፤ “ቡድኔ በራስ የመተማመን ስሜቴ በጣም እንዲጨምር ያደርጋሉ፤ ሁላቸውም በጫዋተው ላይ ትኩረታቸውን ማድረጋቸውን ተመልክቻለሁ፤ አሁን በሻመፒየንስ ሊግ ሙድ ውስጥ ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል።
ካርሎ አንቼሎቲ ሪያል ማድሪድን በአሰልጣኝነት እየመሩ ከከልቡ ጋር የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን በፈረንጆቹ 2014 እና 2022 ላይ ማንሳት መቻላቸው ይታወቃል።
ኤዲን ቴርዚክ
የ41 ዓመቱ የቦርሲያ ዶርትመንድ አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚክ ስለ ጨዋታው በሰጡት አስተያየት፤ “የራሳችን ታሪክ አለን፤ ባለፉት ዓመታት በርካታ የከፍተና የዝቅታ ታሪኮች ነበሩን፤ እያንዳንዱን ጨዋታ ለማሸነፍ የተዋቀረ ቡድን ነን” ብለዋል።
አሁን የሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ ደርሰናል፤ ሻምፒየንስ ሊግን ለማሸነፍ ከተዋቀረ ቡድን ጋር እንጫወታለን፤ ጨዋታውን ለማሸነፍ ሁሉንም እናደርጋለን ብለዋል።
የቡድን ዜና
ሪያል ማድሪድ በዛሬው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ፍፃሜ ጨዋታ ቲቧ ኩርቱዋን በቋሚ አሰላለፍ እንደሚያስገባ አሰልጣኝ ካርሎ አንችሎቲ አረጋግጠዋል።
አሰልጣኝ ካርሎ አንቾሎቲ “አንድሬ ሉኒን የጉንፋን ህመም አጋጥሞት አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው zary ቡድኑን ይቀላቀላል ነገርግን ነገ ኩርቱዋ ቋሚ ይሆናል እሱ ተጠባባቂ ይሆናል” ብለዋል።
ዴቪድ አልባ በጉዳት ምንያት ከስብስቡ ውጪ ሲሆን፤ ለረጅም ጊዜ ከጨዋታ ውጪ የበረው ኤደር ሚልታዎ ለጨዋታ ብቁ መሆኑን ለማስመስከር እየጣረ ይገኛል።
በቦርሲያ ዶርትመንድ በኩል የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ የሆነው በቁርጭምጭሚት ጉዳት ላይ የነበረው አይቮሪኮስታዊው አጥቂ ሴባስቲያን ሀላር ነው።
ጁለየን ዱራንቪል እና ራሜ ባስኔባይኑ ሙሉ በሙሉ ከጀርመኑ ቦርሲያ ዶርትመንድ ስብስብ ውጪ መሆናቸው ቀድሞውኑ የታወቀ ነው።