ኡጋንዳ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ተመን ላይ ቅናሽ አደረገች
ሀገሪቱ የዋጋ ቅናሽ ያደረገችው የዜጎችን የመክፈል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ተብሏል
ኡጋንዳ አንድ ኪሎ ዋት ሀይልን በ0 ነጥብ 2 ዶላር በመሸጥ ላይ ነበረች
ኡጋንዳ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ተመን ላይ ቅናሽ አደረገች፡፡
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ተመን ላይ ማሻሻያ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡
ሀገሪቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ላለፉት 20 ዓመታት የኤሌክትሪክ ሽያጭ ስራን ለግል ኩባንያ ሰጥታ ቆይታለች፡፡
ኩባንያው ለዜጎች መብራት በሚገባ ማሰራጨት አልቻለም እና በየጊዜው የዋጋ ማስተካከያ እያደረገ ነው በሚል ምክንያት ከቀጣዩ መጋቢት ወር ጀምሮ የሀገሪቱ መንግስት ውሉን እንደሚያቋርጥ አስታውቋል፡፡
በመንግስት የተቋቋሙ ሁለት ኩባንያዎችም መብራት የማዳረስ፣ የሀይል መሰረተ ልማቶችን የመገንባት እና ተያያዥ ስራዎችን እንዲሰሩ ቅድመ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ የኡጋንዳ ሀይል ሚኒስትር ሩት ናንካቢርዋ ተናግረዋል፡፡
ሞኒተር የተሰኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ዋት በሰዓት 796 የኡጋንዳ ሽልንግ ወይም 0 ነጥብ 2 ዶላር በመሸጥ ላይ ነው፡፡
መንግስት ከቀጣዩ ሚያዝያ ወር ጀምሮ ሀይል የማሰራጨት ሀላፊነቱን ሲረከብ ይህን የሀይል መሸጫ ተመን ላይ የዋጋ ቅናሽ እንደሚያደርግም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይደረጋሉ ከተባሉ የተመን ማሻሻያ ውስጥ አምራች ኢንዱትሪዎች ብዙ ሀይል በተጠቀሙ ቁጥር የዋጋ ቅናሽ እንዲደረግላቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ብዙ ባመረቱ ቁጥር ኢኮኖሚውን የበለጠ ስለሚደግፉ ይህ አሰራር መዘርጋቱም ተገልጿል፡፡
እንዲሁም አዲሱ መንግስታዊ የሀይል አከፋፋይ ኩባንያ ከዓመታዊ ገቢው ላይ 20 በመቶውን መሰረተ ልማቶቹን ለማዘመን እንዲያውለው ተፈቅዶለታል፡፡
በአጠቃላይ የሐገሪቱ መንግስት በየዓመቱ 70 ሚሊዮን ዶላር ለኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግንባታ ወጪ የማድረግ እቅድ እንዳለውም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡