አወዛጋቢው የኡጋንዳ ጦር አዛዥ ካርቱምን እንቆጣጠራለን ሲሉ ተናገሩ
የፕሬዝደንት ሙሴቬኒ ልጅ የሆነው ጀነራል ኬነሩጋባ ካርቱምን ለመያዝ የፕሬዝደንት ትራምፕን ፕሬዝደንት መሆን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል
ኬነሩጋባ ከሁለት አመት በፊት የኡጋንዳ ጦር ኬንያን በሁለት ሳምንት ውስጥ ይቆጣጠራል የሚል አነጋጋሪ ጽሁፍ አስፍረው ነበር
አወዛጋቢ ንግግሮችን በማድረግ የሚታወቀው የኡጋንዳው ጦር አዛዥ ጀነራል ሙሆዚ ኬነሩጋባ የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምን እንቆጣጠራለን የሚል አዲስ አነጋጋሪ መግለጫ አውጥተዋል።
የፕሬዝደንት ሙሴቬኒ ልጅ የሆነው ጀነራል ኬነሩጋባ በይፋዊ የኤክስ ገጹ ካርቱምን ለመቆጣጠር የፕሬዝደንት ትራምፕን ፕሬዝደንት መሆን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝደንት እስከሚሆን እየጠበቅን ነው። በእሱ ድጋፍ ካርቱምን መቆጣጠር እንችላለን" ብለዋል።
ኬነሩጋባ የሱዳን ጦርነት በቅርቡ ይቆማልም ብሏል።
ኬነሩጌባ ከሁለት አመት በፊት የኡጋንዳ ጦር ኬንያን በሁለት ሳምንት ውስጥ ይቆጣጠራል የሚል አነጋገር ጽሁፍ ማስፈራቸው ይታወሳል።
ኬንያ በኬነሩጋባ ንግግር ቅሬታ ማሰማቷን ተከትሎ ፕሬዝደንት ሙሴቬኒ የልጃቸው ንግግር ያልተገባ መሆኑን በመግለጽ ኬንያን ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ኬነሩጌባ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራትን የተመለከቱ አስተያየቶች የሚሰጡ ሲሆን አንዳንዶቹ ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔ የሚፈጥሩ ናቸው።
ኬነሩጋባ በ2026 በሚካሄደው ምርጫ አባቱን ለመተካት ይወዳደራል የሚል ግምት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ባለፈው ነሐሴ ወር እንደማይወዳደሩ አስታውቋል።
ሀገሪቱን ለ38 አመታት የመሩት ሙሴቬኒ እስካሁን ለውድድሩ እጩነታቸውን ባያረጋግጡም፣ለድጋሚ ምርጫ ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
"በ2026 የምርጫ ወረቀት ላይ እንደማልኖር ላሳውቅ እወዳለሁ" ሲሉ ሙሆዚ ኬነሩጋባ በኤክስ ገጹ አስፍሯል።
"ለቀጣይ ምርጫ ፕሬዝደንት ሙሴቬኒን ሙሉ በሙሉ እደግፋለሁ" ያለው ሞሁዚ ደጋፊዎቹ ሙሴቬኒ ለሰባተኛ ዙር የስልጣን ዘመን እንዲያሸንፉ እንዲመርጣቸው ጠይቋል።
ኡጋንዳን ከ1986 ጀምሮ የመሩት የ80 አመቱ ሙሴቪኒ የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሁለት ጊዜ ህገመንግስት እንዲሻሻል አድርገዋል።
የፖፕ ሙዚቃ ኮከቡን ቦብ ዋይንን ጨምሮ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሙሴቬኔ የጸጥታ ኃይሎችን ተቃዋሚዎችን ለማሰር፣ ለማስፈራራት ወይም ለማሰቃየት ይጠቀሙባቸዋል ሲሉ ይከሷቸዋል። ሙሴቬኒ እነዚህን ክሶች አይሸቀሉም።
በ2021 የተካሄደውን ምርጫ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ዋይኔ የምርጫውን ውጤት አልተቀበለውም። ሙሴቪኒ ግን ምርጫው በጣም ፍትሃዊ የሚባል ነው ይላሉ።