
ካምፓላ በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ለሳልቫ ኪር ድጋፍ መስጠቷ ይነገራል
ኡጋንዳ ወደ ደቡብ ሱዳን ልዩ ሃይል መላኳን አስታወቀች።
የሀገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ የሙሆዚ ካይነሩጋባ ወደ ጁባ የተላኩት ልዩ ሃይሎች ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት "ይጠብቃሉ" ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ኪር እና የምክትላቸው ሬክ ማቻር ውጥረት ተባብሶ ዳግም የእርስ በርስ ጦርነት ሊከሰት ይችላል የሚለው ስጋት አይሏል።
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ ጀነራል ካይነሩጋባ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ "መላውን የደቡብ ሱዳን ግዛት እንደራሳችን ቆጥረን እንጠብቃለን" ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ግን እስካሁን ጀነራሉ ስለሰነዘሩት ሃሳብ ማብራሪያ አልሰጠችም ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
የደቡብ ሱዳን ጦር ምክትል አዛዥ እና ምክትላቸው ባለፈው ሳምንት በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለስልጣናት ማቻር በፈረንጆቹ 2013 ከኪር ጋር ሲዋጉ ለማቻር ድጋፍ ሰጥተዋል።
የማቻር አጋሮች በቁጥጥር ስር መዋል የሰላም ስምምነቱ መጣሱን ያመላክታል የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፍጥነት ተፈተው ውጥረቱ ካልረገበ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል እየተናገሩ ነው።
አንደኛው ሚኒስትር ተቃውሞው ሲበዛ ከእስር መለቀቃቸው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ በላይኛው ናይል ግዛት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች "ዋይት አርሚ" ከሚሰኙ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ከጁባ የሚወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል።
የኪር እና ማቻር የስልጣን ሽኩቻ አዲሷን ሀገር ወደ እርስ በርስ ጦርነት በመክተት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወትን መቅጠፉ የሚታወስ ነው።
ሁለቱ ተፋላሚዎች በ2018 ስልጣን ለመጋራት ተስማምተው ጦርነቱ ቢቆምም ምርጫ አልተካሄደም፤ ታጣቂዎችን በሀገሪቱ ጦር ውስጥ የማዋሃድ እና ህገመንግስቱን የማሻሻል ጉዳዮች ግን በስምምነቱ መሰረት ተፈጻሚ አልሆኑም።