የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ልጅ የሀገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ተቀናቃኝ “አንገት መቅላት” እንደሚፈልጉ ተናገሩ
በአወዛጋቢ ንግግራቸው የሚታወቁት የጦር መሪ የዚህን ሰው ህይወት የታደገው አባቴ ነው ብለዋል
የሀገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ የሆኑት ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ “በእኔ እና ቦቢ ዋይን በተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ መካከል ያለው አባቴ ነው” ብለዋል
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ልጅ የአባታቸውን አስተዳደር ዋነኛ ተቀናቃኝ አንገት መቅላት እንደሚፈልጉ ተናገሩ፡፡
ከ38 ዓመት በላይ ኡጋንዳን ያስተዳደሩት ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ልጅ የሆኑት ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ የሀገሪቱ ዋነኛ ተቀናቃኝ ፓርቲ መሪ ቦቢ ዋይን አንገትን እንዳይቆርጡ የሚከለክሏቸው አባታቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ የሆኑት ኬኒሩጋባ እሁድ አመሻሽ ላይ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “አባቴ ባይኖር ኖሮ የቦቢ ዋይንን አንገት ዛሬውኑ ነበር የምቀላው” ብለዋል፡፡
በ2021 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሙሴቬኒ ቀጥሎ ሁለተኛ ከፍተኛ ድምጽ ባማግኝት ያጠናቀቀው ቦቢ ዋይን በኤክስ ላይ በሰጠው ምላሽ ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎች እንደደረሱበት በመግለጽ ዛቻውን በቀላሉ እንደማይዳልመለከተው ተናግሯል፡፡
ጀነራል ኬኒሩጋባ ለቦቢ ዋይን ምላሽ በድጋሚ ባሰፈሩት ጽሁፍ “በመጨረሻም አነቃሁህ አንገትህን ከመቁረጤ በፊት የተበደርከንን ገንዘብ መልስ” በማለት መንግስት ተቃዋሚዎችን ለማዳከም ባደረጋው ጥረት ቦቢ ዋይንንም በገንዘብ ገዝቶት እንደነበር ለማመላከት ሞክሯል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተደጋጋሚ ጠብ አጫሪ እና አወዛጋቢ ጹሁፎችን በመጻፍ የሚታወቁት የጦር መሪው በ2022 የሀገሪቱ ምድር ጦር ጎረቤት ኬንያን በሁለት ሳምንታት ውስጥ መቆጣጠር እንደሚችል ተናግረው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚሁ አመት በተመሳሳይ ለጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የጋብቻ ጥቃቄ አቅርበው 100 ከብቶችን ጥሎሽ እንደሚሰጡ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር፡፡
የመንግስት ቃል አቀባይ ጀነራሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰነዝሯቸው ሀሳቦች የግላቸው እንጂ የመንግስትን አቋም እንደሚያንጸባርቅ በተደጋጋሚ ማስተባበያ ሰጥቷል፡፡
ከ1986 ጀምሮ ለ4 አስርት አመታት ገደማ ዩጋንዳን እያስተዳደሩ የሚገኙት ዩዌሪ ሙሴቪኒ አልጋ ወራሽ እንደሆኑ በሰፊው ቢገለጽም ጀነራሉ ግን በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሀገሪቱን ዲፕሎማሲ እና ፕሮቶኮል የሚያበላሹ መልዕክቶችን ማጋራታቸውን ቀጥለዋል፡፡