‘ቹይ’ ይባላሉ የተባለላቸው ተሽከርካሪዎቹ ትናንት ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በተገኙበት ይፋ ተደርገዋል
ኡጋንዳ ለምድር ጦሯን መገልገያ የሚሆኑ ዘመናዊ ብረት ለበስ የውጊያ ተሽከርካሪዎችን አመረተች፡፡
ተሽከርካሪዎቹ የምድር ጦሩን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ለማገዝ የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል፡፡
የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የልዩ ዘመቻዎች ከፍተኛ አማካሪ እና የምድር ጦር አዛዥ ሌ/ጄ ሙሆዚ ካይነሩግባ ብረት ለበሶቹ ኡጋንዳ ራሷ ዲዛይን አድርጋ ያመረተቻቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ተሽከርካራቹ ‘ቹይ’ የሚል መጠሪያ እንደተሰጣቸውም ነው ሌ/ጄ ሙሆዚ ያስታወቁት፡፡ ‘ቹይ’ የስዋሂሊኛ ቃል ሲሆን ነብር እንደ ማለት ነው፡፡
የልዩ ዘመቻዎች እና የምድር ጦር አዛዥ ሌ/ጄ ሙሆዚ ካይነሩግባ የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው፡፡
አዳዲሶቹ ብረት ለበሶች ትናንት የ77 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በተገኙበት ይፋ ተደርገዋል፡፡
ሙሴቬኒ ከአሁን ቀደም የተማሩ ኡጋንዳውያን የሚያውቋቸውን ቀላል የፊዚክስ እና የኬሚስትሪ እውቀቶች መተግበር ጀምረዋል ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
ተሽከርካሪዎቹ የኡጋንዳ ጦር አቅም እያደገ ለመሆኑ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ሆኖም ተሽከርካሪዎቹ በምን ዐይነት ግብዓቶች እና ወጪ፤ በምን ያህል መጠንም እንደተመረቱ አልተገለጸም፡፡
ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገራት ታንክን ጨምሮ ሌሎች ብረት ለበስ የውጊያ ተሽከርካራችን በብዛት እስራኤል፣ ዩክሬን፣ ሩሲያ እና ከመሳሰሉ የተለያዩ የውጭ ሃገራት ነው የሚያስገቡት፡፡