ኡጋንዳ በጦር አዛዧ ስርዓተ ቀብር ላይ ሊፈጸም የነበረ የቦምብ ጥቃት ማክሸፏን አስታወቀች
ሜ/ጄ ፓል ሎኬች “የሶማሊያው አንበሳ” በሚለው ቅጽል ስማቸው ይታወቃሉ
ጥቃቱ የሜ/ጄ ፓል ሎኬች የትውልድ ቦታ ተዘጋጅቶ በነበረ ብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ሊፈጸም የነበረ ነው ተብሏል
ኡጋንዳ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ጦር (አሚሶም) ጥላ ስር ሶማሊያ ዘምቶ በነበረው የጦር አዛዧ ስርዓተ ቀብር ላይ ሊፈጸም የነበረ የአጥፍቶ መጥፋት የቦምብ ጥቃት ማክሸፏን አስታወቀች፡፡
የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቱ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ፓደር በተባለች የሜ/ጄ ፓል ሎኬች የትውልድ ቦታ ተዘጋጅቶ በነበረ ብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ሊፈጸም የነበረ ነው፡፡
ሆኖም ጥቃቱ በጸጥታ ኃይሎች ሊከሽፍ እና ካቱምባ አቱል በቅጽል ስሙ “ቤን” ይሰኛል የተባለለት ኡጋንዳዊው ተጠርጣሪ በዋዜማው በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡
ተጠርጣሪው ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ለመስራት ና ለማፈንዳት እንዲሁም አጥፍቶ መጥፋትን ለመፈጸም የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ይዞ መገኘቱን የሃገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
ካቱምባ የቀብር ስነ ስርዓቱን የማወክ ውጥን ይዞ እንደነበርም ነው ቃል አቀባዩ ብርጋዲዬር ፍላቪያ ባይኪያሶ ያስታወቁት፡፡
በአደረባቸው የደም መርጋት ህመም ያሳለፍነው ቅዳሜ በቤታቸው ሳሉ ያረፉት ሜ/ጄ ፓል ሎኬች የአሚሶምን የጸረ አልሸባብ ዘመቻዎች በተለያዩ ጊዜያት መርተዋል፡፡
በዘመቻው ባሳዩትና በሰጡት ቆራጥ አመራርም ጓዶቻቸው “የሶማሊያው አንበሳ” በሚል ይጠሯቸዋል እንደ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ፡፡
በተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎችና የኃላፊነት እርከኖች ሃገራቸውን ያገለገሉት ሎኬች ከ8 ወራት በፊት ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው በፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተሾመውም ነበረ፡፡