ሩሲያ የዘር ፍጅትን ለማስቆም በሚል የጀመረችው 'ወረራ' ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው በሚል እየተከራከረች ነው
ዩክሬን የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የሩሲያን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ ክሷን እንዲሰሙ ጠይቃለች።
ዩክሬን ሩሲያ በፈረንጆቹ 2022 የጀመረችውን ዘመቻ 'የዘር ፍጅትን ለማቆም ነው' ማለቷ ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው ብላለች።
የዩክሬን ተወካይ ለፍርድ ቤቱ "አለመግባባቱን ለመፍታት ስልጣኑ ግልጽ ነው፤ ፍርዳችሁ በአስቸኳይ ያስፈልገናል" ብለዋል።
አክለውም ሞስኮ በ1948 የወጣውን ዓለም አቀፍ የዘር ፍጅት ህግ በመጣሷ ዩክሬን የፍ/ቤቱን ከለላ ትፈልጋለች ሲሉ አሳስበዋል።
ባለፈው ሳምንት ሩሲያ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የዩክሬንን ክስ "ጎደሎ" ነው” በሚል ውድቅ እንዲሆን ጠይቃለች።
ዩክሬን ክሱን ባለፈው ዓመት ጦርነቱ በተጀመረ በቀናት ውስጥ ማቅረቧ ታውቋል።
ኪየቭ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የዘር ፍጅትን ለማቆም በሚል የጀመረችው 'ወረራ' ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው በሚል እየተከራከረች ነው።
ዩክሬን ከ2014 ጀምሮ በሩሲያ የሚደገፉ ኃይሎችን ስትፋለምበት በነበረው በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የዘር ፍጅት ስጋት አልነበረም ስትል ተናግራለች።
ሩሲያ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን የመጀመሪያ ብይን ውድቅ አድርጋለች።
ፍርድ ቤቱ ሞስኮ ወታደራዊ እርምጃዋን እንድታቆም ትእዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን፤ ሆኖም ውሳኔውን የሚያስፈጽምበት ምንም አይነት መንገድ እስካሁን አልተገኘም።