ኡጋንዳ ከሁለት ዓመት በኋላ ትምህርት ቤቶቿን ልትከፍት መሆኑን አስታወቀች
ሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነበር ሁሉንም ትምህርት ቤቶች የዘጋችው
ከጥር ጀምሮ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች እንደምትከፍት ገልጻለች
ኡጋንዳ ከሁለት ዓመት በኋላ ትምህርት ቤቶቿን ልትከፍት መሆኑን ገለጸች፡፡
ሀገሪቱ ትምህርት ቤት የዘጋቸው፣ከሁለት ዓመት በፊት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ነበር፡፡ ዩጋንዳ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሚል ሁሉንም ትምህርት ቤቶቿን መዝጋቷ ይታወሳል፡፡
ከአንድ ወር በኋላ ማለትም ከጥር 10 ቀን 2022 ዓመት ጀምሮ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው ተመልሰው መማር እንደሚጀምሩ የሀገሪቱ ትምህርት ሚኒስትር ጃኔት ካታሃ ለሲጂቲኤን አፍሪካ ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች የተጋነነ የትምህርት ክፍያ እንዳያስከፍሉ የተናገሩት ሚኒስትሩ ወላጆችም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መጎዳታቸውን ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡም ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎቹ በመኖሪያ ቤታቸው በቆዩባቸው ጊዜያት የሬዲዮ ትምህርን ጨምሮ የቤት ውስጥ ትምህርቶችን ሲከታተሉ ቆይተዋል ተብሏል፡፡
የዩንቨርሲቲ እና ኮሌጅ ተማሪዎች ደግሞ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ በማድረግ መመረቃቸወም ተገልጿል፡፡
የኡጋንዳ ፕሬዘዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ከመጭው ጥር ወር ጀምሮ ኢኮኖሚውን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚል የተጣለውን እቀባ በማንሳት ክፍት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎችን የከተበችው ዩጋንዳ ከጥር ወር በፊት ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ሰዎችን የመከተብ እቅድ አስቀምጣለች፡፡