ከሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ጋር በጥምር ባካሄደው ዘመቻ ነው ከተማዋን ነጻ ያወጣው
አሚሶም በአል ሸባብ ጠንካራ ይዞታነት የምትጠቀሰውን የጃናሌ ከተማ ተቆጣጠረ
የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) በአል ሸባብ ጠንካራ ይዞታነት የምትጠቀሰውን የጃናሌ ከተማ መቆጣጠሩን አስታወቋል፡፡
ተልዕኮው ከሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ጋር በመጣመር ባደረገው ዘመቻ ነው ከሞቋዲሾ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 90 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ በታችኛው የሸበሌ ግዛት የምትገኘውን ከተማ ከ3 ቀናት በፊት ነጻ ያወጣው፡፡
አል ሸባብ ጃናሌን በሽብር ተልዕኮዎች ማስፈጸሚያነት ይጠቀምባት ነበር እንደ ተልዕኮው መግለጫ፡፡
30 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ያሏት ከተማዋ አሁን በጥምር ጦሩ ሙሉ ቁጥጥር ስር እንደምትገኝ የኡጋንዳ ደጋፊ ጦር አዛዥ ብሪጋዲዬር ጄነራል ሪቻርድ ኦቶ ተናግረዋል፡፡
ስለ ዘመቻው ስኬታማነት የተናገሩት የተልዕኮው ጦር አዛዥ ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ ይልማ ወንድምሁነኝ በዘመቻው በርካታ የአልሸባብ አባላት መገደላቸውንና መጎዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጥምር ጦሩ በቡድኑ የሚቃጡ ከባባድ ጥቃቶችን ለማስቀረት ስለመቻሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
ለጥምር ጦሩ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክትን ያስተላለፉት ምክትል የተልዕኮው መሪ ሲሞን ሙሎንጎ በበኩላቸው የጃናሌ ነጻ መውጣት ለጸረ ሽብር ዘመቻው ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
በሽብርተኝነት ላይ ተቀዳጀነው ትልቅ ድል ነው ያሉም ሲሆን የቡድኑን ተልዕኮዎች ማክሸፉንና የሃገሪቱ ጦር በጸረ አልሸባብ ዘመቻው የሚጫወቱት የመሪነት ሚና እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡
ጥምር ጦሩ ጃናሌን ነጻ ሊያወጣ የቻለው በተከለሰው የዘመቻዎች ጽንሰ ሃሳብ በመመራት ነው፡፡ እስካሁን ባደረጋቸው ዘመቻዎችም በግዛቱ ጠረፈማ አካባቢዎች የሚገኙ 4 ገደማ ከተሞችን ነጻ አውጥቷል፡፡