ፍቅረኛዋ ቤንዚን አርከፍክፎ ያነደዳት ኡጋንዳዊት አትሌት ህይወቷ አለፈ
በፓሪስ ኦሎምፒክ በማራቶን ሀገሯን የወከለችው አትሌት ሬቤካ ቸፕቴጊ ባለፈው እሁድ ነው በኬንያ ጥቃቱ የደረሰባት
በኬንያ በሴት አትሌቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ መሄዳቸው አሳሳቢ ሆኗል
ኡጋንዳዊቷ የኦሎምፒክ አትሌት ሬቤካ ቸፕቴጊ ህይወቷ ማለፉ ተነገረ።
ቼፕቴጊ ባለፈው እሁድ ኬንያዊው ፍቅረኛዋ ቤንዚን አርከፍክፎ በእሳት ካነደዳት በኋላ ሆስፒታል መግባቷ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የ33 አመቷ አትሌት ከ75 በመቶ በላይ አካሏ ነዶና ሁሉም የሰውነት ክፍሎቿ መስራት አቁመው ህይወቷ ማለፉን በኤልዶሬት ከተማ የሚገኘው ሞይ ሆስፒታል አስታውቋል።
የኡጋንዳ አትሌቲክስ ፌደሬሽንም ቸፕቴጊ ዛሬ ጠዋት ህይወቷ ማለፉን ያረጋገጠ ሲሆን፥ ጥቃቱን አምርሮ አውግዞታል።
በዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ተሳትፋ 44ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ሬቢካ ቸፕቴጊ በምዕራባዊ ኬንያ ለልምምድ በምታቀናበት ወቅት ለማረፊያነት የሚውል ቤት አላት።
አትሌቷ እና ፍቅረኛዋ ከመሬት ጋር በተያያዘ አለመግባባት እንደነበራቸው የአካባቢው ባለስልጣናት ያቀረቡት ሪፖርት ማመላከቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፖሊስ ምርመራው መቀጠሉን ያስታወቀ ሲሆን፥ ጥቃት አድራሹ ኬንያዊ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ውስጥ ይገኛል ተብሏል።
የኡጋንዳ አትሌቲክስ ፌደሬሽን እና የቸፕቴጊ ቤተሰቦች ከቤተክርስቲያን ወደ ቤቷ እንደተመለሰች በቤንዚን ተቃጥላ የሞተችው አትሌት ጉዳይ አፋጣኝ ፍትህ ይሻል ብለዋል።
“እንዲህ አይነት ዘግናኝ ድርጊት በህይወቴ አይቼ አላውቅም” ያሉት አባቷ ጆሴፍ ቸፕቴጊ፥ የልጃቸው ገዳይ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ጠይቀዋል።
በኬንያ በሴት አትሌቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ መሄዳቸው አሳሳቢ ሆኗል።
በ2021 አንገስ ቲሮፕ እና ዳማሪስ ሙትዋ በትዳር አጋሮቻቸው በትራስ ታፍነው እና በስለት ተወግተው ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።