ኡጋንዳዊቷ አትሌት በፍቅረኛዋ በደረሰባት ጥቃት 75 በመቶ አካሏ በቃጠሎ ተጎዳ
ኬንያዊው የአትሌቷ ፍቅረኛ በመካከላቸው በተፈጠረ ጥል ቤንዚን አርከፍክፎ ሰውነቷን እንዳነደደው ፖሊስ አስታውቋል
አትሌቷ በዘንድሮው የፓሪሱ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ነበረች
ኡጋንዳዊቷ የማራቶን አትሌት ሬቤካ ቼፕቴጊ በኬንያ በሚገኘው መኖርያ ቤቷ በፍቅረኛዋ በተፈጸመባት ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት ተነግሯል፡፡
ከኬንያዊው ፍቅረኛዋ ጋር በነበረ አለመግባባት ሰውነቷ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ እሳት የለቀቀባት ሲሆን በዚህም 75 በመቶ የሰውነት አካሏ በቃጠሎው ጉዳት ማስተናገዱን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡
ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ጥንዶቹ ከቤታቸው ውጭ እየተጨቃጨቁ እንደነበር እና ወዲያው ፍቅረኛዋ በእቃ ውስጥ ያለ ፈሳሽ በሰውነቷ ላይ ሲያርከፈክፍ መመልከታቸውን ጎረቤቶች ለፖሊስ ተናግረዋል።
አትሌቷ በአሁኑ ወቅት ኢልዶሬት በተባለ ሆስፒታል ውስጥ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ የትራንስ ናዞይ አካባቢ ፖሊስ አዛዥ ጀረማያ ኦሌኮስዮም ገልጸዋል፡፡
ዳንኤል ኒድያማ የተባለው ጥቃቱን ያደረሰው የአትሌቷ ፍቅረኛ በቃጠሎው መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን፥ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት፡፡
የ33 አመቷ አትሌት ቼፕቴጊ በዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ በማራቶን ሀገሯን የወከለች ሲሆን በውድድሩ 44ተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
ወንጀሉ የተፈጸመው ወደ ኬንያ ለልምምድ በምታቀናበት ወቅት በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል ለማርፊያነት በገዛችው መኖርያ ቤት ውስጥ መሆኑ ታውቋል፡፡
በኬንያ እስከ ሞት የሚያደርሱ በሴት አትሌቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየጨመሩ እንደሚገኙ ከሀገሪቱ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡
በ2022 ሌላኛዋ ሴት አትሌት ዳማሪስ ሙቱዋ በቤቷ ውስጥ በትራስ ታፍና ተገድላ መገኝቷ ይታወሳል፤ በተመሳሳይ ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት የሪከርድ ባለቤት አግነስ ቲሮፕ በስለት ተወግታ ተገድላለች፡፡
ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ኡጋንዳዊው አትሌት ቤንጃሚን ኪፕላጋትም በስለት በደረሰበት ጥቃት ህይወቱ ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡