የኡጋንዳ መዲና ካምፓላ ውጥረት በዝቶባት ውላለች
ሙስና እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ተባብሶ ቀጥሏል በሚል ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል
ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ “ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የውጭ ሃይላት ያስተባበሩት የተቃውሞ ሰልፍ ኡጋንዳን ለማተራመስ ያለመ ነው” ብለዋል
ኡጋንዳ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶችን በቁጥጥር ስር አዋለች።
መዲናዋ ካምፓላ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በርካታ ፖሊስና ወታደሮችን አሰማርታ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይካሄድ መከላከሏን ሬውተርስ ዘግቧል።
ምን ያህል እንደሆኑ ባይጠቀስም የታገደውን ሰልፍ ያደረጉ ወጣቶች ግን ሙስና እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ይቁም የሚሉ መልዕክቶችን የያዙ መፈክሮች ይዘው አደባባይ መውጣታቸው ተገልጿል።
ኤንቲቪ ኡጋንዳ የጸጥታ ሃይሎች ለተቃውሞ የወጡ ውጣቶችን በቁጥጥር ስር አውለው በተሽከርካሪዎች ሲወስዱ የሚያሳይ ምስል ለቋል።
ተቃዋሚዎቹ ወደ ኡጋንዳ ፓርላማ እንዳያመሩ መንገዶች ሁሉ ዝግ ሆነው ካምፓላ የጦር ቀጠና መስላ ውላለች ብሏል ኢድዊን ሙጊሻ የተባለ የከተማዋ ነዋሪ።
የኡጋንዳ ፖሊስ በተቃውሞ ሰልፉ የተሳተፉ ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ማብራሪያ አልሰጠም።
ካምፓላ የተወሰኑ “ወንጀለኛ ወጣቶች” የተቃውሞ ሰልፉን ሽፋን በማድረግ ወደ ዝርፊያ ሊሰማሩ መሆኑን የሚያሳይ የደህንነት መረጃ ደርሶኛል በሚል ሰልፉ እንዳይደረግ ከልክላ ነበር።
ፖሊስ በትናንትናው እለትም የሀገሪቱን ዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲ “ናሽናል ዩኒቲ ፕላትፎርም” ዋና ቢሮ በመክበብ ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ማድረጉን ፓርቲው በኤክስ ገጹ አስታውቋል።
በርካታ የፓርቲው አመራሮችም የተቃውሞ ሰልፉን አስተባብራችኋል በሚል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቁት የፓርቲው መሪ ሮበርት ክያጉላኒ፥ ሰልፉን ባናስተባብርም እንደግፈዋለን ብለዋል።
የ42 አመቱ የቀድሞ ሙዚቀኛ ክያጉላኒ ከ1986 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ዋነኛ ተቀናቃኝ ሆነው ብቅ ካሉ ጥቂት አመታት ተቆጥረዋል።
የሙሴቬኒ አስተዳደር በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መቆጣጠር ተስኖታል የሚሉ ተደጋጋሚ ወቀሳዎች ይቀርቡበታል።
የ79 አመቱ ፕሬዝዳንት በፖለቲካው ታማኝ የሆኑላቸውን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በሙስና መዘፈቃቸውን እያወቁ በዝምታ ማለፋቸውንም ተቃዋሚዎቻቸው ያነሳሉ።
የሚነሳባቸውን ተቃውሞ ከምዕራባያን ሴራ ጋር የማገናኘት ልምድ ያላቸው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒል፥ ባለፈው ቅዳሜም ለዛሬ ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ ከምዕራባውያን ጋር አስተሳስረውት ነበር።
“ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከውጭ ሃይላት ጋር ሆነው ባስተባበሩትና ኡጋንዳን የማተራመስ ተልዕኮ ባለው ሰልፍ ላይ እንዳትሳተፉ” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውንም ሬውተርስ አስታውሷል።