ኡሁሩ ኬንያታ፤ ብሊንከን ናይሮቢ ከመግባታቸው ከአንድ ቀን በፊት ለምን አዲስ አበባ መጡ?
ነገ ሰኞ ህዳር 6 ቀን 2014 ዓ/ም ናይሮቢ እንደሚገቡ የሚጠበቁት አንቶኒዮ ብሊንከን ኬንያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሃገራትን ይጎበኛሉ
ኬንያታ ነገ ሰኞ በናይሮቢ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከንን ይቀበላሉ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት ላይ ከተገኙ የአፍሪካ ሃገራት መሪወች መካከል አንዱ የሆኑት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንደነበር ተሰምቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም "ዉድ ወንድሜ ፕሬዚደንት ኡኹሩ ኬንያታ ወደ ሁለተኛዉ ቤትዎ እንኳን ደህና መጡ" ሲሉ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ራሳቸው ነገ በመዲናቸው ናይሮቢ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከንን ይቀበላሉ፡፡
ነገ ሰኞ ህዳር 6 ቀን 2014 ዓ/ም ናይሮቢ እንደሚገቡ የሚጠበቁት አንቶኒዮ ብሊንከን ኬንያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሃገራትን ይጎበኛሉ፡፡ ብሊንከን እንደሚጎበኟቸው የሚጠበቁት ሃገራትም ናይጄሪያ እና ሴኔጋልን ናቸው፡፡
የብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝት እስከ ህዳር 11 ቀን 2014 ዓ/ም የሚዘልቅ ነው፡፡
በመሆኑም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ብሊንከንን ከመቀበላቸው ከአንድ ቀን በፊት ለምን ወደ ኢትዮጵያ መጡ? ታስቦበት ወይስ የአጋጣሚ ጉዳይ የሚለው እስካሁን አልታወቀም፡፡ በሁለቱ መንግስታት በኩል የተገለጸም ነገርም የለም፡፡
በቅርቡ ወደ ዋሽንግተን ተጉዘው ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በኋይት ሃውስ የተወያዩት ኬንያታ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መነጋገራቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያውያን ግጭቱን ለማስቆም ይወያዩ ሲሉ ከሰሞኑ የማሳሰቢያ ጥሪ ማቅረባቸውም አይዘነጋም፡፡ የዛሬው የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ብሊንከንን ከማግኘታቸው በፊት የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ለመረዳትና ከሃገሪቱ መሪዎች ጋር ለመመካከር እንደሚሆንም ይገመታል፡፡
ብሊንከንም ቢሆኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር የስልክ ቆይታዎችን ከማድረግ በዘለለ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን ሲሰጡ ነበር፡፡
የሰሞኑ የአፍሪካ ጉብኝታቸው በዚሁ ዙሪያ ሊያጠነጥን እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡ ጉብኝቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሲመት ላይ ወደተገኙ የሃገራት መሪዎች ነው የሚደረገው፡፡
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት መሃመዱ ቡሃሪ እንዲሁም የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በበዓለ ሲመቱ ተገኝተው እንደነበር አይረሳም፡፡
ከዚህ ባለፈ ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ኬንያ የኢትዮጵያ ጎረቤትና ጥብቅ ግንኙነት ያላት የጥንት ወዳጅ ስትራቴጂያዊ አጋርም ናት፡፡
ናይጄሪያ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የትውልድ ሀገር ናት፡፡ በፕሬዝዳንትነት እንደመሯትም ይታወቃል፡፡
ሴኔጋል ደግሞ ቀጣይዋ ማለትም የ2022 የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ናት፡፡ በትረ ስልጣኑንም በመጪው ጥር በሚካሄደው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትረከባለች፡፡