የብሪታኒያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዊኪሊክስ መስራቹ ዩሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ወሰነ
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲፈጸም በብሪታኒያ ሃገር ውስጥ ሚኒስቴር መጽደቅ አለበት
ፍርድ ቤቱ አሜሪካ አሳንጅ በቅጡ ሊዳኝ የሚችልባቸውን ዋስትናዎች አቅርባለች ብሏል
የብሪታኒያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዊኪሊክስ መስራቹ ዩሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ወሰነ፡፡
የአሳንጅ የአዕምሮ ጤና የአሜሪካን የወንጀል ምርመራ ስርዓት ለመቋቋም በሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም በሚል በስር ፍርድ ቤት ተሰጥቶ የነበረውን ውሳኔ የሻረው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ወስኗል፡፡
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አሜሪካ አሳንጅ በቅጡ ሊዳኝ የሚችልባቸውን በቂ ዋስትናዎች ማቅረቧን ገልጿል፡፡
በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቱ ዳኛ ተከሳሹ ተላልፎ እንዲሰጥ ለሃገር ውስጥ ሚኒስቴር ጥያቄ እንዲያቀርብ አዟል፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚኒስቴሩ ይሁኝታ ያሻል፡፡
ሆኖም የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ አቤቱታ ሊቀርብ እንደሚችል ነው የተከሳሹን ጠበቃ እና የቅርብ ሰዎች ዋቢ ያደረጉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የዘገቡት፡፡
የአሳንጅን ተላልፎ መሰጠት የተቃወሙ በርካቶች እንዲለቀቅ ጠይቀዋል፡፡
የዊኪሊክስ መስራቹ አሳንጅ ወታደራዊ መረጃዎችን ጨምሮ በርካታ ሚስጥሮችን አጋልጧል፡፡
አሜሪካ የአፍጋኒስታን እና የኢራቅ ዘመቻዎቿን በተመለከተ ከ10 ዓመታት በፊት ካጋለጠው ሚስጥራዊ ወታደራዊ መረጃ ጋር በተያያዘ ነው አሳንጅን የምትፈልገው፡፡ ሰልሎኛል በሚልም በ17 ክሶች ከስሳዋለች፡፡
እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ክሶቹ እስከ 175 ዓመታት የሚያስፈርዱ ናቸው ምንም እንኳን እስካሁን የተላፈው ረዥሙ የእስር ጊዜ 63 ወራት ቢሆንም፡፡