በግድቡ ዙሪያ የሶስትዮሽ ድርድሩን መጀመር እንደሚደግፉ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ
ጆንሰን ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል
ጠ/ሚ ቦሪስ ብሪታኒያ የሀገራቱን ወደ ውይይት መመለስ ታግዛለች ብለዋል
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ቦሪስ ጆንሰን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አለመግባባት ውስጥ ያሉት ሶስቱ ሀገራት ድርድር እንዲጀምሩ እንደሚደግፉ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከግብጹ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር የስልክ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
መሪዎቹ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የፕሬዝዳንት ሲሲ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ባሳም ራዲ መግለጻቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
በውይይቱ ስለ ኢንቨስትመንት ትብብር፣ ስለ ጤና፣ ጸጥታና ሽብርተኝነት መነጋገራቸውንም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
ግብጽ በናይል ውኃ ላይ “ታሪካዊ መብት” እንዳላትና ይህንንም እንደምታስከብር የገለጹት ፕሬዝዳንት ሲሲ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሃገራቱ የጀመሩትን የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥሉና ሁሉን አቀፍ፣ ትክክለኛ እና አሳሪ (አስገዳጅ) ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሀገራቱ ወደ ውይይት እንዲመለሱ ብሪታኒያ እንደምታግዝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግብጽ በየጊዜው የምታነሳውንና በናይል ውሃ ላይ አለኝ የምትለውን “ታሪካዊ የውኃ መብት” እንደማትቀበልና አሳሪ ስምምነትንም እንደማትቀበል በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ የውኃ ክፍፍል ጉዳይ አሁን መነሳት እንደሌለበትና መነሳት ካስፈለገም፤ ክፍፍሉ መሆን ያለበት በሶስቱ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት መካከል መሆን እንዳለበት መግለጿ አይነጋም፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ከትናንት በስቲያ ሰኞ ሃምሌ 12 ቀን 2013 ዓ/ም ተጠናቋል በሚል በመንግስት መገለጹም የቅርብ ጊዜ ተውስታ ነው፡፡