ዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ በነፍስ ወከፍ 215 ሽህ ዶላር መደበች
የጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ ወግ አጥባቂ መንግስት ከሩዋንዳ ጋር ባደረገው ስምምነት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ሊመልስ ነው
እርምጃው ከፈረንሳይ በትናንሽ ጀልባዎች የሚነሱ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመከላከል ነው
ብሪታንያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያቀደችው እቅድ በነፍስ ወከፍ 169 ሽህ ፓውንድ (215 ሽህ ዶላር) እንደሚያስወጣት ገለጸች።
ይህ የተባለው በትንንሽ ጀልባዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ለመቀነስ መንግስት ባወጣው የመጀመሪያ ዝርዝር ግምገማ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ ወግ አጥባቂ መንግስት ባለፈው ዓመት ከሩዋንዳ ጋር ባደረገው ስምምነት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ስድስት ሽህ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ሀገር መላክ ይፈልጋል።
የእንግሊዝ መንግስት ከፈረንሳይ በትናንሽ ጀልባዎች የሚነሱ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመከላከል እቅዱን እንደ ሁነኛ አድርጎ ያየዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሱናክ ከወግ አጥባቂ ህግ አውጭዎች እና ከህዝቡ ጉዳዩን እንዲፈቱ ግፊት የተደረገባቸው ሲሆን፤ ከአምስቱ ቀዳሚ ጉዳዮቻቸው ውስጥ አንዱ አድርገውታልም።
የሀገር ውስጥ ሚንስትር ሱኤላ ብራቨርማን ወጪው ወደ ብሪታንያ ለመድረስ የሚሞክሩትን ሌሎችን ከመከልከልና ከመኖሪያ ቤት ዋጋ መጨመር ጎን ለጎን ግምት ውስጥ መግባት አለበት ብለዋል።
እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ የመኖሪያ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወጪ በዓመት ከሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ፓውንድ ወደ 11 ቢሊዮን ፓውንድ ከፍ ይላል ሲሉም አክለዋል።
"የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ግምገማው ምንም ነገር አለማድረግ አማራጭ እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል" ሲሉም ተናግረዋል።