አለቶች በበዙባት የግሪክ ደሴት ወንድ ልጅ የተገላገለችው ኤርትራዊት ስደተኛ
የግሪኳ ደሴት ሌስቦስን ስደተኞች ወደ አውሮፓ ዘልቀው ለመግባት ይመርጣሉ
ኤርትራዊቷ ስደተኛ “አስፈላጊውን የህክምና እንክብካቤ” እየተደረገላት መሆኑም ተገልጿል
አንድ ኤርትራዊት ስደተኛ አለቶች በበዙባት የግሪኳ ሌስቦስ ደሴት ወንድ ልጅ እንደተገላገለች የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።
ኤርትራዊት ስደተኛ ልጅ ተገላገለችው አብረዋት ከነበሩና ከቱርክ የመጡ ሌሎች ስደተኞች ጋር በጉዞ ሳለች ነው ተብሏል።
አንድ ግሪክ የባህር ጥበቃ ባለስልጣን እንዳስታወቁት፤ ከቱርክ ተነስተው ባህር በማቋረጥ በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ሌስቦስ ደሴት በኩል ወደ ግሪክ ሊገቡ የነበሩት ስደተኞች 29 ሲሆኑ ከስደተኞቹ ልጅ የተገላገለችውን ጨምሮ አምስቱ ሴቶች ናቸው፡፡
ወንድ ልጅ የተገላገለችው እንስት አሁን ላይ በደሴቱ በሚገኝ ሆስፒታል አስፈላጊውን የህክምና እንክብካቤ እየተደረገላት ነው ያሉት ባለስልጣኑ፤ የተቀሩት ስደተኞች በሌስቦች እንዲቆዩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
"እናትና ልጁ በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸውም" ብለዋል፡፡
ክስተቱን ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው መልእክት ያጋሩት የግሪክ የትራንስፖርት ሚኒስትር ጂያኒስ ፕላኪዮታኪስ “ በህገዋጥ እና ስነ-ምግባር በሌላቸው አሻጋሪዎች በደሴቱ ተጥላ ልጅ የወለደቸውን ስደተኛ ህይወት ያዳናችሁ የግሪክ ባህር ጥበቃ አባላትና ኃላፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡
የግሪኳ ሌስቦስ ደሴት ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለይም እንደፈረንጆቹ ከ2015 እስካ 2016 በነበሩ ጊዜያት ፤ በጦርነት ምክንያት ከኢራቅ እና ሶሪያ የሸሹትን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲጠቀሙባት እንደነበረ ይታወቃል፡፡
አሁንም ኤርትራውያንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ስደተኞች ወደ አውሮፓ ዘልቀው ለመግባት የሚመርጧት ደሴት ናት።