ቻይና የአውሮፓን ቴክኖሎጂ በመስረቅና ሩሲያን ትደግፋለች ሲሉ ሱናክ ከሰዋል
የብሪታንያ እጩ ጠቅላይ ሚንስትር ቻይናን በጠላትነት ፈረጁ።
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ከፓርቲያቸው እና ከስራ ባልደረቦቻቸው በደረሰባቸው ጫና ስልጣን እለቃለሁ ማለታቸው ይታወሳል።
ይሄንን ተከትሎም ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት 11 እጩዎች ቀርበው በመጨረሻም የህንድ ዝርያ ያላቸው ሪሺ ሱናክ እና ሊዝ ትሩስ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል።
የብሪታንያ ፋይናንስ ሚንስትር የሆኑት እና አሁን ላይ ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት በመጨረሻ ትንቅንቅ ላይ የሚገኙት ሪሺ ሱናክ ምርጫውን አሸንፈው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ከሆኑ በቻይና ላይ ማዕቀቦችን እንደሚጥሉ ተናግረዋል።
ቻይና የአውሮፓን እና የብሪታንያ ቴክኖሎጂዎችን እየሰረቀች ነው የሚሉት እጩ ጠቅላይ ሚንስትሩ በስልጣን ዘመናቸው ቻይና ለፋብሪካዎቿ ከብሪታንያ የምትገዛቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዳይደርሷት አደርጋለሁ ሲሉም ተናግረዋል።
እጩ ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ቻይና ዩክሬንን ከወረረችው ሩሲያ ነዳጅ በገፍ በመግዛት ድጋፍ እያደረገች እንደሆነም ገልጸዋል።ቻይና ከዚህ በፊት እጩ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ ከሌሎች እጩዎች ጋር ሲነጻጸሩ የተሻሉ መሪ እንደሆኑ ተናግራ ነበር።
እጩ ጠቅላይ ሚንስትር ሱናክ በምርጫው ካሸነፉ በብሪቴን ያሉ ከ30 በላይ የቻይና ባህል ማዕከላትን እንደሚዘጉም ዝተዋል።
ቻይና ከቴክኖሎጂ ወረራዎች ባለፈ በባህል እና ሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ተጽዕኖ እየፈጠረች ነው የሚሉት ሱናክ ይህን በብሪታንያ ምድር እንዲከወን አልፈቅድም ሲሉም ተናግረዋል።
ቦሪስ ጆንሰንን የሚተኩት ጠቅላይ ሚንስትር በፈረንጆቹ መስከረም 5 ቀን 2022 የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ያሳውቃል ተብሏል።