ሪሺ ሱናክ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ተረጋገጠ
ሪሺ ሱናክ በብሪታንያ ታሪክ የሕንድ ዝርያ ያለው የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሏል
ዳግም ወደ ስልጣን ሊመጡ ይችላሉ የተባሉት ቦሪስ ጆንሰን ለሪሺ ሱናክ ሲሉ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸውን ተናግረዋል
የ42 ዓመቱ ቀድሞው የፋይናንስ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ተረጋግጧል።
ለስድስት ሳምንታት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሊዝ ትሩስ ስልጣን እንደሚለቁ መናገራቸውን ተከትሎ ከአራት በላይ የብሪታንያ ፖለቲከኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ወደ ውድድር ገብተው ነበር።
ሪሺ ሱናክ፣ ቦሪስ ጆንሰን፣ ፔኒ ሞርዳንት፣ እና ሌሎችም የብሪታንያ ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ድጋፍ ወደ ማሰባሰብ ቢገቡም አሁን ላይ ከሪሺ ሱናክ ውጪ ሁሉም እጩዎች ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸው ተገልጿል።
ይሄንን ተከትሎም ከህንድ ቤተሰብ የተገኙት ባለጸጋው ሪሺ ሱናክ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ተረጋግጧል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሪሺ ሱናክ የብሪታንያ ንጉስ ቻርልስ የስልጣን መልቀቂያ ያስገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስን ተክተው መንግስት እንዲመሰርቱ ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑም ተገልጿል።
በሁለት ወራት ውስጥ ሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ያስተናገደው የብሪታንያ መንግስት በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ሲሆን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዋነኝነት ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ዋነኛ ስራቸው እንደሚሆን ተገልጿል።
በቀድሞው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አስተዳድር ውስጥ በፋይናንስ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ሪሺ ሱናክ በብሪታንያ ታሪክ የሕንድ ዝርያ ያለው የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉም ተብሏል።
ሪሹ ሱናክ ትምህርታቸውን በኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ በፋይናንስ አስተዳድር የተከታተሉ ሲሆን በኮሮና ቫይረስ ወቅት የብሪታንያ ኢኮኖሚ እንዳይጎዳ ጥሩ አበርክቶ እንደነበራቸው ተገልጿል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ በፊት በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቻይና የብሪታንያ ጠላት እንደሆነች እና በመሪነት ከተመረጡ ቻይና የብሪታንያን ቴክኖሎጂ እንዳትጠቀም ማዕቀብ እጥላለሁ ማለታቸው ይታወሳል።