ብሪታንያ የእርዳታ ፕሮግራሟን የሰረዘችው ኢኮኖሚዋ እንዲያገግም በማሰብ እንደሆነ ገልጻለች
ብሪታንያ ከሶስት ዓመት በፊት የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት ወቅት ኢኮኖሚዋን ከባሰ ጉዳት ለመጠበቅ በሚል የውጭ ሀገራት እርዳታ እንዲቆም ወስና ነበር።
ለሁለት ዓመት በሚል ተጥሎ የነበረው ይህ እገዳ በዚህ ዓመት የሚጠናቀቅ ቢሆንም አዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ እገዳው እንዲራዘም መወሰናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ብሪታንያ አግዳው የነበረውን የውጭ ሀገራት እርዳታ ፕሮግራም እንዲራዘም የወሰነችው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከኮሮና ቫይረስ ጉዳት አላገገመም በሚል ነው።
እንዲሁም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ የነዳጅ እና ምግብ ዋጋ ብሪታንያን ጨምሮ በዓለም ሀገራት መጨመሩ ለእርዳታ እገዳው መራዘም ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
ከአንድ ሳምንት በፊት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ሪሺ ሱናክ የፋይናንስ ሚንስትር በነበሩበት ወቅት የብሪታንያ የውጭ ሀገራት እርዳታ ፕሮግራም እንደ ፈረንጆቹ 2024 ላይ ዳግም እንደሚጀመር ተናግረው ነበር።
ይሁንና ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ የብሪታንያ የውጭ ሀገራት እርዳታ ፕሮግራም እስከ 2027 ድረስ እንዲራዘም ወስነዋል ተብሏል።
የብሪታንያ ኢኮኖሚ በተለይም ከአውሮፓ ህብረት በህዝበ ውሳኔ ከወጣችበት 2016 ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረዶችን እያስተናገደ ሲሆን ሀገሪቱ በገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት አምስት ጠቅላይ ሚንስትሮችን አስተናግዳለች።
ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንን የተኩት ሊዝ ትሩስ ስልጣን በተረከቡ ከስድስት ሳምንታት በኋላ በምርጫ ወቅት የገባሁትን ቃል መፈጸም አልቻልኩም በሚል ስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።