በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት መሬት ለመቀማት ሳይሆን የዓለምን ስርዓት ለመቀየር የሚደረግ ጦርነት ነው ተብሏል
እንግሊዛዊያን ለአይቀሬው ጦርነት እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀረበ፡፡
የብሪታንያ ጦር ዋና አዛዥ ዜጎች ከሩሲያ ጋር ለሚደረገው ጦርነት እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በለንደን በተካሄደ ወታደራዊ ተሸከርካረ ዎች አውደ ርዕይ ላይ ንንግር ያደረጉት ጀነራል ሰር ፓትሪክ ሳንደርስ ሩሲያ ብሪታንያን ማጥቃቷ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት የተሰራው መዘናጋት ብሪታንያን ዋጋ አስከፍሏል ያሉት አዛዡ በዩክሬን ላይ እየደረሰ ያለው ክስተት ለዚህ አንድ ማሳይ ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ብሪታንያዊያን ለጦርነት እንዲዘጋጁ የሚያደርግ የሰው ሀይል ዘመቻ እንደሚያሰፈልግም ዋና አዛዡ በንግግራቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡
"አያቶቻችን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተዘናግተው ዋጋ ከፍለዋል፣ አሁን ያለው ትውልድም ይህ ከመሆኑ በፊት ሊዘጋጅ ይገባል" ያሉት ጀነራል ሰር ፓትሪክ ሳንደርስ የሩሲያ ዩክሬን ወረራን አሳንሶ ማየት ስህተት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አዛዡ አክለውም "በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የሩሲያ ኢምፓየር የመገንባት አልያም ዶምባስን የመጠቅለል ጉዳይ አይደለም፣ ጦረነቱ ከስርዓታችን ጋር ነው" ሲሉም በአውደ ርዕዩ ላይ ያልተጠበቀ ንግግር አድርገዋል፡፡
ብሪታንያ የጦሯን አቅም አሁን ካለው በእጥፍ ማሳደግ አለባት ያሉት አዛዡ በቀጣይ ተጨማሪ ብሪታንያዊያንን ወደ ጦሩ ለመቀላቀል ስራዎች እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
የብሪታንያ ጦር በተለመደው የወታደራዊ ምልመላ መንገድ ተገቢውን የሰው ሀይል ካላገኘ በዘመቻ ዜጎች ወደ ውትድርና እንዲቀላቀሉ ሊደረግ እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
የጦር አዛዡን ንግግር ተከትሎ አስተያየት የሚሰጡ ብሪታንያዊያን መጨመሩን ተከትሎ መንግስት በቅርቡ ዜጎችን በገፍ ወደ ውትድርና የማስገባት እቅድ እንደሌለው አስታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ብሪታንያ በተለመደው ባህላዊ የሆነውን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የወታደሮች ምልመላ ስርዓትን እንደሚከተል ተናግለዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአውሮፓ ሀገራት የጦር አዛዦች ዜጎቻቸው ለጦርነት እንዲዘጋጁ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ሲሆኑ ከሰሞኑ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር የሩሲያ ኔቶ ጦርነት በቀጣዮቹ አመታት መነሳቱ አይቀሬ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ኔቶን ለመቀላቀል ጫፍ ላይ የደረሰችው ስዊድን ጦር አዛዥም ስዊድናዊያን ጦርነት ወደ ደጃቸው እየመጣ ነው ልትዘጋጁ ይገባል ሲሉ ንግግር ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡