ዩክሬን በሩሲያ ላይ የሳይበር ጥቃት የፈጸሙ አካላትን አመሰገነች
ኬቭ ለመረጃ መንታፊዎች በይፋ የምስጋና ምስክር ወረቀት በመላክም የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች
እውቅናው የመረጃ ስርቆትን በሀገር ደረጃ ማበረታታት ነው በሚል ተተችቷል
ዩክሬን በሩሲያ ላይ የሳይበር ጥቃት የፈጸሙ አካላትን በይፋ አመሰገነች።
የሀገሪቱ ጦር የሩሲያን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለሰለሉና መረጃ ለመነተፉ ግለሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀት መላኩም ተሰምቷል።
“ዋን ፊስት” የአሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ፖላንድን ጨምሮ የስምንት ሀገራት ዜግነት ያላቸው የመረጃ መንታፊዎችን ያካተተ ቡድን ነው።
ቡድኑ በሩሲያ ላይ በርካታ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ማድረጉን የቡድኑ አባላት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ሲያጋሩ ቆይተዋል።
የመረጃ መንታፊ ቡድኑ ከሩሲያ የመከላከያ ተቋማት መረጃ በመስረቅና የወታደሮች እንቅስቃሴ ቅኝት የሚደረግባቸው የደህንነት ካሜራዎችን በመጥለፍ ለኬቭ መረጃ ሲያጋራ መቆየቱ ተገልጿል።
የዩክሬን አየርሃይል አዛዥም ለቡድኑ ስምንት አባላት ፊርማቸው ያረፈበት የምስጋና የምስክር ወረቀት መላካቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከቡድኑ አባላት መካከል “ቮልቴጅ” በሚል ስያሜ የሚታወቀውና በአሜሪካ ሚቺጋን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰራው ክሪስቶፈር ኮርትራይት ይገኝበታል።
የ53 አመቱ ክሪስቶፈር ዩክሬን ያደረገውን ጥረት በመመልከት የእውቅና ምስክር ወረቀት መላኳ እንዳስደሰተው ይናገራል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተችበት የካቲት 2022 ጀምሮ ከሞስኮ ወሳኝ መረጃዎችን ለመስረቅ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን የሚያነሳው ግለሰቡ “ዩክሬን ድል እንድታደርግ ስራዬን እስከማጣት ደርሻለሁ” ይላል።
“ዋን ፊስት” ከሩሲያ መንትፎ ለዩክሬን ካጋራቸው መረጃዎች ውስጥ ሩሲያ በክሬሚያ ከርች ድልድይ በኩል በርካታ ታንኮችን ማሻገሯን የተመለከተው ይገኝበታል። ይህንምም ያደረገው በክሬሚያ የሚገኙ የደህንነት ካሜራዎች በመጥለፍ መሆኑን ክሪስቶፈር ይገልጻል።
ባለፈው ጥር ወርም ክሪስቶፈር እና በጎፈቃደኛ መረጃ መንታፊዎቹ የሩሲያን ዋነኛ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያ 100 ጊጋባይት ሚስጢራዊ መረጃ በመስረቅ ለዩክሬን አሳልፈው መስጠታቸውም የኬቭ ባለስልጣናትን ማስፈንደቁ አይዘነጋም።
ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ጀምሮ በጎፈቃደኛ የመረጃ መንታዎች በሩሲያ ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ ስታበረታታ የቆየችው ዩክሬን በይፋ ለእነዚህ አካላት እውቅና መስጠቷ አነጋጋሪ ሆኗል።
ኬቭ ለመረጃ መንታፊዎች በይፋ የምስጋና የምስክር ወረቀት በመላክም የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።
አሜሪካና ብሪታንያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት “ሀላፊነት ለሚሰማቸው የመረጃ መንታፊዎች” እውቅና የሚሰጥበትን ስርአት ቢዘረጉም እንደ ኬቭ እስካሁን በይፋ ሲያመሰግኑ አልታየም።
ሩሲያም “ኪልኔት” የተሰኘው የመረጃ መንታፊ ቡድን በዩክሬን ላይ ተመሳሳይ የሳይበር ጥቃት እንዲፈጽም እየሰራች ነው የሚሉ ዘገባዎች ቢወጡም እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠችም።
“የሳይበር ደህንነት ፍልስፍና” የተሰኘ መጽሃፍን የጻፉት ዶክተር ሉካስ ኦሌጅኒክ፥ ኬቭ ለውጭ የመረጃ መንታፊዎች የሰጠችው እውቅና ችግር አደገኛ ነው ብለዋል።
በጄኔቫ ኮንቬንሽን የተቀመጠውን መርህ የሚጥስና የግለሰቦችን የመረጃ ስርቆት በሀገር ደረጃ እንደማበረታታት የሚታይ ነው ሲሉም ተቃውመውታል።