አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ250 ሚሊየን ዶላር የጦር መሳርያ ድጋፍ አደረገች
በሩስያ ውስጥ ጥቃት ለማድረስ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ለመጠቀም የጠየቀችው ፍቃድ ውድቅ ተደርጓል
የአሜሪካው የመከላከያ ሚንስትር የረጅም ርቀት ሚሳኤሎቹ የጦርነቱን ውጤት አይቀይሩትም ብለዋል
አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ250 ሚልየን የጦር መሳርያ ድጋፍ ማጽደቋን አስታወቀች።
በትንትናው እለት የዩክሬኑ ፕሬዝዳነት ቮለደሚር ዘለንስኪ ከአውሮፓ አጋሮቻቸው እና ከአሜሪካ የመከላከያ ሚንስትር ጋር በጀርመን ተገናኝተዋል።
በውይይቱ ጦርነቱን ለማስቆም በሩስያ ላይ ተጨማሪ ጫናዎች እንዲደረጉ ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በሩስያ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም እንዳይውሉ የተከለከሉትን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ለመጠቀም ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሩስያ ዋና የአየር ማዘዣ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ነው በረጅም ርቅት ሚሳኤሎች ላይ የተጣለው ክልከላ እንዲነሳ የጠየቁት።
የአሜሪካው የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን ለዚህ በሰጡት ምላሽ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን በሩስያ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም ጥቅም ላይ ማዋል የጦርነቱን ውጤት አይቀይረውም ብለዋል።
በሩስያ ውስጥ የሚገኙ ግዙፍ ኢላማዎችን ለማጥቃት ካስፈለገም ዩክሬን የራሷን ድሮኖች መጠቀም ትችላለች ነው ያሉት።
ሚንስትሩ በዚህ ውግያ በራሱ ወሳኝ የሚሆን የተለየ አቅም የለም የሩስያን ጥቃት ለመመከት የሚያስፈልገው የተቀናጀ ጥቃት እና ስትራቴጂ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኬቭ በሩስያ ውስጥ ጥቃት ከመሰንዘር ይልቅ በድንበሯ ውስጥ እየገፋ የሚገኝውን የሞስኮ እግረኛ ጦር አቅምን ማሽመድመድ ላይ ብታተኩር መልካም ይሆናል ያሉት የመከላከያ ሚንስትሩ፤ አሜሪካ ለዚህ ዘመቻ የሚያግዝ ተጨማሪ የ250 ሚሊየን የጦር መሳርያ ድጋፍ ማድረጓን አስታውቀዋል።
ከአሜሪካ በተጨማሪ ጀርመን 12 ከባባድ መድፎችን የሰጠች ሲሆን ካናዳ 80 ሺህ ከአየር ላይ የሚተኮሱ ሮኬቶችን በመጪዎቹ ወራት ለመስጠት ቃል ገብታለች፡፡
ዩክሬን በምዕራባዊ ሩስያ ከርሰክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ወደ ፊት ለመጓዝ ጥረት እያደረገ ሲሆን ሩስያ በበኩሏ በጦርነቱ የዩክሬን ዋነኛ የሎጂስቲካ መተላለፍያ የሆነችውን ፖክሮቨስክ ከተማን መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጋለች፡፡