ቁልፍ ወደተባለችው ፖክሮቭስክ ከተማ እየገፋች ያለችው ሩሲያ አንድ ከተማ መቆጣጠሯን አስታወቀች
የሩሲያ ኃይሎች ከአሜሪካ ኦሀዮ ግዛት ጋር እኩል የሚሆነውን 1/5ውን የዩክሬን ግዛት ተቆጣጥረዋል
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የሩሲያ ወታደሮች ከወሳኟ የፖክሮቭስክ ከተማ 12 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ኖቮሮዲቪካ ከተማን ይዘዋል
ቁልፍ ወደተባለችው ፖክሮቭስክ ከተማ እየገፋች ያለችው ሩሲያ አንድ ከተማ መቆጣጠሯን አስታወቀች።
ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ወደአላት የምስራቅ ዩክሬኗ ፖክሮቭስክ ከተማ እየገፉ ያሉት እና የዩክሬንን ምሽግ ለመስበር የሚፈልጉት የሩሲያ ኃይሎች አንድ ከተማ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን ሩሲያ በትናንትናው እለት አስታውቃለች።
ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ ከአሜሪካ ኦሀዮ ግዛት ጋር እኩል የሚሆነውን ወይም የዩክሬንን 1/5 የተቆጣጠሩት የሩሲያ ኃይሎች የዶምባስ ግዛትን ሙሉ በሙሉ ለመያዝ በምስራቅ ዩክሬን ወደፊት እየገፉ ናቸው።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የሩሲያ ወታደሮች ወሳኝ የሎጅስቲክ ማስተላለፊያ ከሆነችው የፖክሮቭስክ ከተማ 12 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ኖቮሮዲቪካ ከተማን ይዘዋል። ከተማዋ 14 ሺ ህዝብ ይኖርባት ነበር።
በዩክሬን የተወለደው ተጽዕኖ ፈጣሪ የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ ደጋፊ የሆነው ዩሪ ፖዶሊያካ የተባለው ጸኃፊ የሩሲያ ኃይሎች ከከተማዋ አልፈው ለፖክሮቭስክ ሰባት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሲያጠቁ የሚያሳይ ካርታ ፖስቷል። ሮይተርስ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላደር ፑቲን ዩክሬን ድንበር ጥሳ ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት መግባቷ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የምታደርገውን ግስጋሴ ማስቆም አልቻለም ብለዋል። ነገርግን የዩክሬን ከፍተኛውን ወታደራዊ አዛዥ የኩርስክ ጥቃት ስኬታማ መሆኑን እና ሩሲያ በፖክሮቭክ ቀጣና ባለፉት ስድስት ቀናት ወደፊት እንዳልገፋች ተናግሯል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ዩክርስክ ዘመቻ ዋና አላማ የሩሲያ ኃይሎች ወደፊት እንዳይገፉ ለማድረግ እንደነበር ገልጸዋል። ሩሲያ አሁን ላይ 80 በመቶ የሚሆነውን የዶምባስ ግዛት ተቆጣጥራ ትገኛለች።
የሩሲያ ጦር በምስራቅ ዩክሬን በፍጥነት እየገፋ መሄዱ ሊቆረጥ የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል የሚል ስጋት እንዳላቸው አንዳንድ የሩሲያ የጦር ጸኃፊዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ፑቲን በ10ሻዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን "ለልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ወደ ዩክሬን ያሰማሩት በፈረንጆቹ የካቲት 2022 ነበር።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ፣ የሩሲያን ኃይሎች እንደሚያሸንፉ እና እንደሚያባርሩ ዝተዋል።
ዩክሬን የሩሲያን ጥቃት ለመከላከል ምዕራባውያን የአየር መከላከያ እንዲሰጧት እና የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ተጠቅማ ሩሲያው ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ እንዲፈቅዱላት እየተማጸነቻቸው ትገኛለች።