የዩክሬን ጦር ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮች ይፈልጋል - ዜለንስኪ
ከምዕራባውያን የሚደረጉ ድጋፎች የተቀዛቀዙባት ኬቭ ከፍተኛ የተተኳሽ ጥይት ችግር ገጥሞኛል ብላለች
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሁለተኛ አመቱን ለመያዝ ተቃርቧል
የዩክሬን ጦር ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮች እንዲቀርቡለት መጠየቁን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ በኬቭ በሰጡት መግለጫ፥ ወታደራዊ አዛዦች ከ450 እስከ 500 ሺህ የሚደርስ ወታደር ይቅረብልን የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን አንስተዋል።
አስቸጋሪ እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው ላሉት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም ዝርዝር ማብራሪያ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን ነው ያብራሩት።
ዩክሬን በአሁኑ ወቅት ከ500 ሺህ በላይ ወታደሮቿ ከሩሲያ ጦር ጋር እየተዋጉ ይገኛሉ ተብሏል።
ኬቭ ከምዕራባውያን የምታገኘው ድጋፍ በተቀዛቀዘበት ወቅት ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮችን ወደ ግንባር ለማሰማራት የምትችል ግን አይመስልም።
የአሜሪካ ኮንግረንስ ለዩክሬን ሊደረግ የነበረ የ60 ቢሊየን ወታደራዊ ድጋፍ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረትም ለዩክሬን ሊያደርገው ያቀደው የ55 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ በሃንጋሪ ውድቅ መደረጉ አይዘነጋም።
አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ህብረት ኬቭን እንዲሁ አንተዋትም ቢሉም እንደቀድሞው ከፍ ያለ ወታደራዊ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ግን አይጠበቅም።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ሁለተኛ አመቱን ለመያዝ በተቃረበበት ወቅት ዩክሬን ከፍተኛ የተተኳሽ ጥይት ችግር እንዳለባት ገልጻለች።
የፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ሚስት ኦሌና ዜሌንስካ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ “ዩክሬናውያን ያለ ምዕራባውያን ድጋፍ ህልውናቸው የመቀጠሉ ጉዳይ አሳሳቢ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ በበኩሏ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” የሚል ስያሜ የሰጠችውን ጦርነት እንደምትገፋበትና 617 ሺህ ወታደሮቿ በዩክሬን ውጊያ ላይ መሆናቸውን ገልጻለች።
ሁለቱም ሀገራት ጦርነቱ በድርድር እንዲቆም አሁን ላይ ፍላጎት እንደሌላቸው መሪዎቻቸው ተናግረዋል።