ሩሲያ፤ በዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ ያለው ውጥረት እንዲቀንስ “ዓለም በዩክሬን ላይ ጫና ማድረግ አለበት” አለች
ክሬምሊን፤ የዩክሬን ጦር ግዙፉን የኒውክሌር ጣቢያ ለማውደም ተኩስ ከፍቷል በማለት በቅርቡ ኪቭን መክሰሷ የሚታወስ ነው
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ዩክሬን መላውን አውሮፓ አደጋ ላይ እየጣለች ነው” ብለዋል
ክሬምሊን፤ በዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ አከባቢ ያለውን ወታደራዊ ውጥረት እንዲቀንስ “ዓለም በዩክሬን ላይ ጫና ማድረግ አለበት” ሰትል ጥሪ አቀረበች።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሰራተኞች ወደ ጣቢያው ጉዞ እያደረጉ ባለበት ወቅት፤ ዩክሬን በጣቢያው ዙሪያ ያለውን ውጥረት እንዲባበስ በማድረግ መላው አውሮፓ አደጋ ላይ እየጣለች ነው ሲሉ ከሰዋል።
ቃል አቀባዩ፤ ይህን ይበሉ እንጅ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው አከባቢ ከጦር ነጻ እንዲሆን በተባበሩት መንግስታትም ሆነ በአሜሪካ ቀደም ብሎ ሲቀርብ ስለነበረው ጥሪ የሩሲያ ፍላጎት እንዳልሆነ በመመስል አኳሃን ምላሽ መስጠታቸውም ሮይተርስ ዘግቧል።
ሞስኮ “አሜሪካ እንምትለው የኒውክሌር ጣቢያው ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ነጻ ስለማድረግ እየተናገረች አይደለም” ነገር ግን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኪቭ ላይ ጫና መፍጣር አለበትም ብለዋል።
ሩሲያ፤ የዩክሬን ጦር ግዙፉን የኒውክሌር ጣቢያ ለማውደም ተኩስ ከፍተዋል በማለት በቅርቡ ኪቭን መክሰሷ የሚታወስ ነው።
ዩክሬን ግዙፉን አቶሚክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ማውደሟ “አሰቃቂ መዘዝ” ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ልታውቅ ይገባል ስትል ማስጠንቀቋም እንዲሁ አይዘነጋም።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የዛሬ ሶስት ሳምንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "የዩክሬን ታጣቂ ሃይሎች የኒውክሌር ጣቢያን ማውደም ከዩክሬን ባለፈ ለአውሮፓ ምድር እጅግ አደገኛ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው”ሲሉ ተደምጠዋል።
የዩክሬን አጋሮች "እንዲህ ዓይነቱ የዩክሬን እርምጃ እንዳይቀጥል ተጽእኖ ያድርጉ" ሲሉም ጠይቀው ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው እለት ወደ ኒውክሌር ጣቢያው ማቅናቱ የተገለጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጠሪ ቡዱን ፤ ወደ ጣቢያው በሚጓዝበት ወቅት ምንም አይነት እንቅፋት እንዳይገጥመው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያሳሰበ ነው።
የቡድን-7 አባል ሀገራት ዳይሬክተሮች ቡዱን ባወጣው መግለጫ፤ ሰራተኞቹ "ያለ ምንም እንቅፋት" መድረስ መቻል አለባቸው ሲል አሳስቧል።
በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን የሚገኘው ዛፖሪዝሂያ አቶሚክ ሃይል ማመንጫ በአውሮፓ ትልቁና በዓለም ላይ ካሉት 10 ትላልቅ የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች መካከል አንዱ ነው።
እናም በጦርነት ውስጥ የሚገኙትና እርስ በርስ የሚካሰሲት ሩሲያና ዩክሬን በጣቢያው ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከሀገራቱ በዘለለ ለተቀረው ዓለም ያልተፈለገ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ ተሰግቷል።