የዩክሬን ጦር ባለፈው ሳምንት በምዕራባዊ ሩሲያ የጀመረውን ዘመቻ መቀጠሉ ተነግሯል
በሩሲያ ኩርስክ ክልል ዘልቆ የገባው የዩክሬን ጦር 1 ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር (100 ሺህ ሄክታር) የሩሲያን ግዛት መቆጣጠሩን ገለጸ።
የዩክሬን ጦር ከፍተኛ አዛዥ ኦሌክሳንደር ስይርስኪ እንዳስታወቁት ባለፈው ሳምንት የሩሲያን ድንበር ጥሶ የገባው የዩክሬን ጦር እያካሄደ የሚገኘውን ዘመቻ ቀጥሏል።
ሩሲያ ከዚህ ቀደም ሀገራትን በመውረር ጦርነት ትከፍት ነበር ያሉት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ፥ አሁን ጦርነት ወደራሷ ግዛት መጥቶላታል የሚል መግለጫ ከቀናት በፊት ሰጥተዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን ይህን የዩክሬን ጦር ድንበር ጥሶ መግባት “ከባድ ጸብ አጫሪነት” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፥ የሀገራቸው ጦር ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ከዩክሬን ጋር በሚዋሰኑ ሶስት የሩሲያ ክልሎች የሚገኙ ከ121 ሺህ በላይ ሰዎች በውጊያው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከመኖሪያቸው እንዲለቁ ተደርጓል።
የዩክሬን ጦር 28 መንደሮችን መቆጣጠሩን የሚገልጹት የኩርስክ ክልል አስተዳዳሪ፥ ተጨማሪ 56 ሺህ ዜጎች ከቀያቸው እንዲወጡ ታዘዋል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ወደ ሩሲያ ግዛት 30 ኪሎሜትሮችን ዘልቆ መግባቱ የተነገረለት የዩክሬን ጦር በትናንትናው እለት ጉይቮ በተባለች መንደር የዩክሬንን ሰንደቅ አላማ ሲሰቅል የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ወደ ሀገሪቱ ግዛት ዘልቆ የገባውን የዩክሬን ጦር ከሰባት ቀናት በኋላም ማስወጣት አልቻለም።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ግን የሩሲያ ጦር የሚሰጠው ምላሽ “ሩቅ አይሆንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ዩክሬን በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿንና በርካታ ታንኮችና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ወደ ምዕራባዊ ሩሲያ በማስገባት ዘመቻ የከፈተችው ሩሲያን አስገድዳ ወደ ድርድር ለማምጣት በማሰብ ነው ተብሏል።
ክሬምሊን ግን የዩክሬን ጦር ድንበር ጥሶ መግባቱ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን በመጥቀስ “ጸባ አጫሪ ድርጊቱ” ለድርድር በር የሚከፍት አይደለም ብሏል።