ዩክሬን ሶስት የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖችን መትቼ ጥያለሁ አለች
“ኤስዩ -34” የጦር አውሮፕላኖቹ በኬርሰን ግዛት መውደቃቸውን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናግረዋል
ሞስኮ ስለጦር አውሮፕላኖቿ መመታት አስተያየት አልሰጠችም
ዩክሬን የሩሲያን ሶስት የጦር አውሮፕላኖች መትታ መጣሏን አስታወቀች።
“ኤስዩ - 34” ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በጦርነት ቀጠና ውስጥ ባለችው ኬርሰን ግዛት ተመተው መውደቃቸውንም ነው የሀገሪቱ ጦር የገለጸው።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የሩሲያን የጦር አውሮፕላኖች መትተው ለጣሉ ዩክሬናውያን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአውሮፕላኖቹ መመታት በዩክሬን ድብደባ የሚፈጽሙ አብራሪዎች “ያለቅጣት ወደመጡበት እንደማይመለሱ” ያስጠነቅቃቸዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ሞስኮ እስካሁን ስለጦር አውሮፕላኖቿ መመታት አስተያየት አልሰጠችም።
የሩሲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ግን አደጋው መከሰቱን እየዘገቡ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል።
የጦር አውሮፕላኖቹ በአሜሪካ ሰራሹ ፓትሪዮት ሚሳኤል ሳይመቱ አልቀረም የተባለ ሲሆን፥ ከአብራሪዎቹ ውስጥ የሞቱና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው እንዳለም ተገልጿል።
ሁለተኛ አመቱን ለመድፈን በተቃረበው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ኬቭ በርካታ የጦር አውሮፕላኖቿ ወድመውባታል።
በሞስኮ የተያዙ ግዛቶቿን ለማስመለስ ለምታደርገው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻም ከምዕራባውያን ተዋጊ ጄቶች እንዲቀርቡላት መመጻኗን ቀጥላለች።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ በትናንት ምሽቱ መግለጫቸው አሜሪካ ሰራሹን “ኤፍ - 16” የጦር አውሮፕላን ከሆላንድ ለመቀበል ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ከአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ልታገኘው የነበረው ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ሳይጸድቅላት የቀረችው ዩክሬን ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ችግር እንደገጠማት ማሳወቋ የሚታወስ ነው።