አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ 1 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ልታደርግ ነው
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኬቭ ጉብኝት ሲያደርጉ ነው ድጋፉን ይፋ ያደረጉት
ሩሲያ የዋሽንግተን የጦር መሳሪያ ድጋፍ የሚለውጠው ነገር የለም ብላለች
አሜሪካ ለዩክሬን የ1 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባች።
ከአዲሱ ድጋፍ ውስጥ 665 ሚሊየን ዶላሩ ለጦር መሳሪያዎች ግዥ ይላል ተብሏል።
አሜሪካ ለዩክሬን ፀረ ሚሳኤሎች፣ ታንኮች እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን እንደምትልክም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒ ብሊንከን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ ትናንት በዩክሬን ያልተጠበቀ ጉብኝት ሲያደርጉ ድጋፉ የኬቭን መልሶ ማጥቃት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ከአዲሱ የ1 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ 175 ሚሊየን ዶላሩ በቀጥታ ለዩክሬን መከላከያ ማጠናከሪያ የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለስንኪ በበኩላቸው ሀገራቸው በቀጣይ ወራት ፈተና ሊገጥማት ስለሚችል ወታደራዊ ድጋፉ እንዲጠናከር ብሊንከንን ነግረዋቸዋል።
አሜሪካ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለኬቭ ከ70 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች።
ይሁን እንጂ ኬብ ከሰኔ ወር ጀምሮ ግዛቶቿን ከሩሲያ ለማስለቀቅ የጀመረችው መልሶ ማጥቃት የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አላስገኘም።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዩክሬን ጉብኝትም የተቀዛቀዘውን መልሶ ማጥቃት ለማነቃቃት ያለመ ነው ተብሏል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ግን የብሊንከን ጉብኝትም ሆነ የ1 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ ድጋፉ የሩሲያ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም ብለዋል።
በተያያዘ አሜሪካ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በማውደም ውጤታማ ናቸው የሚባልላቸውን ከዩራኒየም የሚሰሩ ተተኳሾችንም ለመላክ መወኗን ፔንታጎን አስታውቋል።
የእነዚህ ጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋል አከራካሪ ነው።