ግድያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ቃለመሀላ ከመፈጸማችው አስቀድሞ እንዲከናወን ታቅዶ እንደነበርም ተገልጿል
ዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪን የመግደል ሴራን አከሸፍኩ አለች።
በሩሲያ ተመልምለው መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ የዩክሬን ብሄራዊ ዘብ አገልግሎት አባላትም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የዩክሬን የስለላ ተቋም (ኤስቢዩ) ያስታወቀው።
የተቋሙ ሃላፊ ቫስይል ማልዩክ በቴሌግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ የሩሲያ የደህንነት አገልሎት (ኤፍኤስቢ) ፕሬዝዳንት ዜለንስኪን እና ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን ለማስገደል ሴራ ሲሸርብ መቆየቱን ደርሰንበታል ብለዋል።
የከሸፈው የግድያ ሙከራ በዛሬው እለት ቃለመሃላ ለፈጸሙት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኬቭ የሚቀርብላቸው “ስጦታ” ይሆናል በሚልም ተሳልቀዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ዩክሬን የፕሬዝዳንቱና ሌሎች ኢላማ የተደረጉ የግድያ ሙከራ ማክሸፏ የሩሲያ የደህንነት ተቋም ውድቀት ማሳያ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን ጦርነት ከመክፈቷ በፊት መልምላቸዋለች የተባሉት ሁለት ዩክሬናውያን ወታደሮች በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ዝርዝር ጉዳይ አልተጠቀሰም።
ሞስኮ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ዩክሬናውያን የመለመለችው ለፕሬዝዳንቱ ቅርበት ያላቸው ጠባቂዎች በመሆናቸው ነው ብሏል የዩክሬን የደህንነት ተቋም።
ወታደሮቹ ከዜለንስኪ ጋር በሚንቀሳቀሱበት ወቅትም የሚገኙበትን ትክክለኛ የቦታ አቅጣጫ (የጂፒኤስ መረጃ) ለሩሲያ መላካቸውን የጠቀሰው ተቋሙ፥ ሞስኮ ይህን መረጃ ስለመጠቀሟ ግን አላብራራም።
በዩክሬን መከላከያ፣ ደህንነት እና ሌሎች ተቋማት ውስጥ የሚሰሩና ለሩሲያ የሚሰልሉ የሀገሪቱን ዜጎች “ከሃዲዎች” ሲሉ የገለጿቸው የዩክሬኑ የስለላ ተቋም ሃላፊ ቫስይል ማልዩክ፥ ለሞስኮ ሚስጢራዊ መረጃዎችን የሚያጋሩ አካላት ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ ሲሉ ዝተዋል።
ዩክሬን ከዚህ ቀደምም ፕሬዝዳንት ዜለንስኪን ለመገድል ሴራ ሲሸርቡ ነበር ያለቻቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሏን መግለጿ ይታወሳል።
ባለፈው ወርም ከሩሲያ የስለላ ተቋም ጋር በመተባበር ዜለንስኪን ለመግደል ሲንቀሳቀስ ነበር የተባለ ፖላንዳዊ መያዙ አይዘነጋም።
ፓወል ኬ የተባለው ፖላንዳዊ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በፖላንድ የሚጠቀሟቸውን አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ተያያዥ መረጃዎችን ለሞስኮ አሳልፎ ሲሰጥ ነበር ተብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ከኬቭ ለሚቀርቡ ወቀሳዎች ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በዝምታ ማለፍን መርጧል።