ሩሲያ ፈረንሳይና ብሪታኒያ በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ሰጡትን አስተያየት “አደገኛ “ በማለት ፈረጀች
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንትና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለ ዩክሬን ጦርነት አስተያየት ሰጥተዋል
የሩሲያ ጦር የፈረንጆቹ 2024 ከተጀመረ የመጀመሪያ ወራት 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፍራን በመቆጣጠሩን አስታውቋል
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት እና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት ሩሲያ “አደገኛ ነው” በማለት ፈረጀች።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በዩክሬን ጦርነት ላይ የሰጡት አስተያየት በግጭቱ ዙሪያ ያለውን ዓለም አቀፍ ውጥረት የሚያባበስ መሆኑን ክሬምሊን አስተውቋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባሳለፍነው ሃሙስ በሰጡት አሰተያየት ላይ ወታሮችን ወደ ዩክሬን የመላኩን ጉዳይ አሁንም በድጋሚ ማንሳታቸው ተነግሯል።
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በተመሳሳይ ቀን ኪቭን በጎበኙበት ወቅት፤ ዩክሬን ሩሲያን ለማጥቃት የብሪታኒያ የረጅም ርቀት መሳሪያዎችን መጠቀም ትችላለች ማለታው ተሰምቷል።
የሩሲያ ቤተ መንግስት ክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በዚህ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የፕሬዝዳንት ኢማኑል ማክሮንን ንግግር “በጣም ወሳኝ እና በጣም አደገኛ መግለጫ” በማለት ገልጸውታል።
በጦርነቱ ውስጥ የፈረንሳይ ቀጥተኛ ተሳትፎን በተመለከተ የማክሮን አስተያየት “በጣም አደገኛ አዝማሚያ" ነው ሲሉም ቃል ዘቀባዩ ገልጸዋል።
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ዩክሬን በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን ለማጥቃት የብሪታኒያ የውጭ የረጅም ርቀት መሳሪያዎችን መጠቀም እንደምትችል መግለጻቸውም “ሌላኛው አደገኛ መግለጫ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አስተያየቶቹ በዩክሬን ግጭት ዙሪያ ቀጥተኛ ውጥረቶችን የሚያባብስ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ይህም የአውሮፓን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልና መላውን የአውሮፓ የደህንነት መዋቅር የሚያናጋ ነው ብለዋል።
በተያያዘ ዜና ሩሲያ በጦር ግንባር ድልን እየቀዳጀች መሆኑን እና በርካታ ስፍራዎችን ከዩክሬን በማስለቀቅ እየተቆጣጠረች መሆኑን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ስርጌ ሼይጉ በሰጡት መግለጫ፤ የፈረንጆቹ 2024 ከተጀመረ ወዲህ ባሉ የመጀመሪያ ወራት የሩሲያ ጦር 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፍራን ከዩክሬን ጦር በማስለቀቅ መቆጣጠሩን ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት፤ የዩክሬን ጦር ከምስራቃዊ ዶኔስክ አከባቢ ለቀው በመውጣት ላይ እንደሚገኝ መግለጻው ይታወሳል።
ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ አክለውም ዩክሬን ጦር የሚያስፈለግውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከአሜሪካ ከማግኘቱ በፊት ሩሲያ ያላትን የወታደርና የጦር መሳሪያ ቁጥር ብላጫ በመጠቀም ቦታዎችን እየተቆጣጠረች መሆኑንአስታውቀዋል።
አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ለዩክሬን የ61 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኗ ይታወቃል።
ሆኖም ግን የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፎች የዩክሬን ወታደሮች በጦር መሳሪያ እጥረት እየተቸገሩ ያሉበት የጦር ግንባሮች ለመድረስ ገና ጊዜ ይወስድባቸዋል ነው የተባለው።