ሚኒስትሩ ኬቭ ከምዕራባውያን ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ እንድታገኝ አድርገዋል
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ሬዝኒኮቭ ከስልጣናቸው ለመልቀቅ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተነገረ።
ሚኒስትሩ ከሃላፊነታቸው እንደሚነሱና በዚህ ሳምንትም የሀገሪቱ ፓርላማ እርሳቸውን የሚተካ ሰው እንደሚሾም ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ትናንት ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ሚኒስትሩ በዛሬው እለትም የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ነው የተገለጸው።
ከህዳር 2021 ጀምሮ የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ሬዝኒኮቭ ኬቭ ከምዕራባውያን ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንድታገኝ ማድረጋቸው ተገልጿል።
በተለይ ጀርመን ሊዮፓርድ 2 የተሰኘውን ታንክ ለዩክሬን እንድትሰጥ በማግባባቱ ረገድ ትልቅ አበርክቶ ነበራቸው ተብሏል።
ከጥር 2022 ወዲህ ግን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የሚመሩት መስሪያ ቤት በሙስና መዘፈቁን ሲያነሱ ከርመዋል።
ሬዝኒኮቭ በግላቸው ሙስና ውስጥ ስለመዘፈቃቸው ባይነገርም የመከላከያ ሚኒስቴሩ ግን በተለያዩ የማጭበርበር ወንጀሎች ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል።
የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያሳየው ዩክሬን በአለማቀፉ የሙስና ደረጃ ከ180 ሀገራት 116ኛ ደረጃን ይዛለች።
ሙስናን የመታገሉ ዘመቻ ኬቭን የአውሮፓ ህብረት አባል ለማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ሀገርአቀፍ ዘመቻ መክፈታቸውን ያስታወቁት ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የመከላከያ ሚኒስትሩን ከሃላፊነት ለማንሳት የወሰኑበትን ምክንያት ይፋ አላደረጉም።
ሬውተርስ እንደዘገበው ከስልጣናቸው የሚነሱት ሬዝኒኮቭ ኦሌክሲ በለንደን የዩክሬን አምባሳደር ሆነው ይሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዩክሬን የፕራይቬታይዜሽን ፈንድ ሃላፊው ሩስተም ሬዝኒኮቭ ሬዝኒኮቭን ይተካሉ ተብሏል።