ጥቃቱ ላይ ከዩክሬን ምንም አይነት አስተያየት አልተሰጠም
የሩሲያ ባለስልጣናት ዩክሬን ፍንዳታ ያስከተለ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት በማዕከላዊ ሞስኮ ማድረሷን ተናግረዋል።
የሞስኮ ከንቲባ ሰርጌይ ሶቢያኒን የአየር መከላከያዎች ሰው አልባ አውሮፕላኑን በጥይት መትተው ፍርስራሾቹ በከተማዋ ኤግዚቢሽን ማዕከል ላይ መውደቁን አስታውቀዋል።
ጥቃቱ በሩሲያ ዋና ከተማ ላይ የደረሰ የተመሳሳይ ጥቃቶች የቅርብ ጊዜው ነው ተብሏል።
በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ ምስል በሞስኮ ሰማይ ግራጫ ጭስ አሳይቷል።
ጉዳዩ ላይ ከዩክሬን ምንም አይነት አስተያየት አልተሰጠም። ነገር ግን የኪየቭ ባለስልጣናት በሞስኮ ላይ ጥቃት መፈጸሙን በይፋ አምነው አያውቁም።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር የአየር መቃወሚያ ስርዓቱ ሲከፈት ድሮኖች የበረራ አቅጣጫቸውን ቀይረው መውደቃቸውን ተናግሯል።
ድሮኖቹ የመኖሪያ አካባቢ ባልሆነው የመንግስት ህንጻዎች በሚበዙበት ማዕከላዊ ሞስኮ መውደቃቸው ተገልጿል።
በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ሚንስቴሩ ጠቅሷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
የኤግዚቢሽኑ ማዕከል ለጉባኤ እና ለስብሰባዎች የሚያገለግል ግዙፍ ቦታ ሲሆን፤ ከክሬምሊን ከአምስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።
በአካባቢው የነበረ አንድ እማኝ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ጥቃቱ "ኃይለኛ ፍንዳታ" አድርሷል ብሏል።