ኪየቭ ትልቅ የዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ጥምረት ለመገንባት ኢላማ አድርጋለች ተብሏል
በዩክሬን ያለውን ጦርነት በሰላማዊ እልባት ለማስቆም ያለመ የሰላም ንግግር በሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ተጀምሯል።
40 የሚጠጉ ሀገራት ተወካዮች እየተሳተፉበት ባለው ንግግር ኪየቭ ተጨማሪ ሀገራት የሰላም እቅዷን እንዲደግፉ እያግባባች ነው ተብሏል።
ዩክሬን እና አጋሮቿ በጂዳ በጀመሩት የብሄራዊ ደህንነት አማካሪዎች እና የ40 ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ምክክር ጦርነቱን ማስቆም በሚቻልበት ቁልፍ መርሆዎች ላይ እንደሚስማሙ ተስፋ ተደርጓል።
የኬቭ የልዑካን ቡድን መሪ "ንግግሩ ከባድ እንደሚሆን እጠብቃለሁ። ግን እውነት ከጎናችን ናት፤ መልካምነት ከእኛ ጋር ነው" ብለዋል።
ንግግሩ ሩሲያን አያካትትም። ነገር ግን ክሬምሊን ስብሰባውን "በቅርብ እከታተላለሁ" ብሏል።
ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት ቻይና ለድርድሩ ልዩ መልዕክተኛዋን ሊ ሁዋን እንደምትልክ ማስታወቋ ይታወሳል።
ልዩ መልዕክተኛው "ብዙ አለመግባባቶች አሉን እና የተለያዩ አቋሞችን ሰምተናል። ነገር ግን የእኛ መርሆች የጋራ መሆናቸው አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
ጦርነቱ እየተባባሰ በመምጣቱ እና ኪየቭ በመልሶ ማጥቃት ግዛቷን ለማስመለስ በምትጥርበት ወቅት፤ የዩክሬን፣ ሩሲያ እና ዓለም አቀፍ ባለስልጣናት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ወገኖች መካከል ቀጥተኛ የሰላም ድርድር ሊኖር የሚችልበት ተስፋ አይታየንም ብለዋል።
ነገር ግን ዩክሬን በመጀመሪያ ከምዕራባውያን ደጋፊዎቿ ባለፈ ትልቅ የዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ጥምረት ለመገንባት ኢላማ አድርጋለች።
እንደ ህንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ በጦርነቱ ገለልተኛነታቸውን ያሳዩ ደቡባዊው ሀገራትን አጋርነት ለማግኘት አይኗን ጥላለች።